ዘሌዋውያን 23:15-21 NASV

15 “ ‘የሚወዘወዘውን የነዶ መሥዋዕት ካቀረባችሁበት የሰንበት ማግስት አንሥታችሁ ሰባት ሙሉ ሳምንታት ቊጠሩ።

16 እስከ ሰባተኛው ሰንበት ማግስት ድረስ አምሳ ቀን ቊጠሩ፤ ከዚያም የአዲስ እህል ቊርባን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርቡ።

17 በሁለት ዐሥረኛ የኢፍ መስፈሪያ የላመ ዱቄት፣ በእርሾ የተጋገረ ሁለት እንጀራ ለሚወዘወዝ መሥዋዕት፣ የበኵራት ስጦታ እንዲሆን ከየቤታችሁ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አምጡ።

18 ከእንጀራውም ጋር ሰባት ነውር የሌለባቸው የአንድ ዓመት ተባዕት የበግ ጠቦቶች፣ አንድ ወይፈንና ሁለት አውራ በጎች አቅርቡ፤ እነዚህም ከእህል ቊርባናቸውና ከመጠጥ ቊርባናቸው ጋር ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናሉ፤ ይህም በእሳት የሚቀርብ ሽታውም እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት ነው።

19 እንዲሁም አንድ ተባዕት ፍየል ለኀጢአት መሥዋዕት፣ ሁለት የአንድ ዓመት ተባዕት ጠቦቶችም ለኅብረት መሥዋዕት አቅርቡ።

20 ካህኑም ሁለቱን የበግ ጠቦቶች ከበኵራቱ እንጀራ ጋር የሚወዘወዝ መሥዋዕት አድርጎ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ይወዘውዛቸዋል፤ እነዚህም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ቅዱስ መሥዋዕት፣ የካህኑም ድርሻ ናቸው።

21 በዚያኑ ዕለት የተቀደሰ ጉባኤ ዐውጁ፤ የተለመደ ተግባራችሁንም አታከናውኑ፤ ይህም በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ለሚመጡት ትውልዶች የዘላለም ሥርዐት ነው።