21 በዚያኑ ዕለት የተቀደሰ ጉባኤ ዐውጁ፤ የተለመደ ተግባራችሁንም አታከናውኑ፤ ይህም በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ለሚመጡት ትውልዶች የዘላለም ሥርዐት ነው።
22 “ ‘የምድራችሁን መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ፣ የዕርሻችሁን ዳርና ዳር አትጨዱ፤ ቃርሚያውን አትልቀሙ፤ እነዚህንም ለድኾችና ለእንግዶች ተዉላቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።’
23 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
24 “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘የሰባተኛው ወር የመጀመሪያ ቀን ዕረፍት ይሁንላችሁ፤ በዚሁ በመለከት ድምፅ የሚከበር የተቀደሰ ጉባኤ ይኑራችሁ።
25 መሥዋዕትን በእሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርቡ እንጂ የተለመደ ተግባራችሁን አታከናውኑበት።’ ”
26 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
27 “የሰባተኛው ወር ዐሥረኛ ቀን የስርየት ቀን ነው፤ የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ አንዳች ነገርም አትብሉ፤ መሥዋዕትም በእሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርቡ።