2 “ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ወደምሰጣችሁ ምድር በምትገቡበት ጊዜ ምድሪቱ ራስዋ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ሰንበት ታክብር።
3 ስድስት ዓመት በዕርሻህ ላይ ዝራ፤ ስድስት ዓመት ወይንህን ግረዝ፤ ፍሬውንም ሰብስብ።
4 በሰባተኛው ዓመት ግን ምድሪቱ የዕረፍት ሰንበት ታድርግ፤ ይህም የእግዚአብሔር (ያህዌ) ሰንበት ነው። በዕርሻህ ላይ አትዝራ፤ ወይንህንም አትግረዝ።
5 ሳይዘራ የበቀለውን አትጨደው፤ ካልተገረዘው የወይን ተክልህ ፍሬ አትሰብስብ። ምድሪቱ የአንድ ዓመት ዕረፍት ታድርግ።
6 ምድሪቱም በሰንበት ጊዜዋ የምታስገኘው ማንኛውም ፍሬ ለአንተ፣ ለወንድ ባሪያህ፣ ለሴት ባሪያህ፣ ለቅጥር ሠራተኛህና ከአንተ ጋር ለሚኖር መጻተኛ ምግብ ይሁን፤
7 እንዲሁም ለቤት እንስሶችህና በምድርህ ለሚኖሩ የዱር አራዊት ምድሪቱ የምታበቅለው ሁሉ መኖ ይሁን።
8 “ ‘ሰባት የሰንበት ዓመታት ማለትም ሰባት ጊዜ ሰባት ዓመታትን ቊጠር፤ ሰባቱ የሰንበት ዓመታትም አርባ ዘጠኝ ዓመታት ይሆናሉ።