12 “ ‘መሥዋዕቱ ፍየል ከሆነ፣ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያቅርብ፤
13 በራሱም ላይ እጁን ይጫንበት፤ በመገናኛው ድንኳን ፊት ለፊት ይረደው፤ የአሮንም ልጆች ደሙን በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ይርጩት።
14 ከሚያቀርበውም መሥዋዕት ላይ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት የሚቀርብ ቊርባን አድርጎ ያቅርብ፤ የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ሥብ፣ ከሆድ ዕቃው ጋር የተያያዘውን ሥብ ሁሉ፣
15 ሁለቱን ኵላሊቶች፣ በኵላሊቶቹ ላይና በጐድኑ አጠገብ ያለውን ሥብ፣ እንዲሁም የጒበቱን መሸፈኛ ከኵላሊቶቹ ጋር አብሮ አውጥቶ ያቅርብ።
16 ካህኑም ይህን ሁሉ በእሳት የሚቀርብና ሽታውም ደስ የሚያሰኝ የመብል ቊርባን አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያቃጥል፤ ሥብ ሁሉ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ነው።
17 “ ‘በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ፣ ሥብ ወይም ደም ከቶ አትብሉ፤ ይህ ለመጪው ትውልድ ሁሉ የተሰጠ የዘላለም ሥርዐት ነው።’ ”