ዘሌዋውያን 3:8-14 NASV

8 በጠቦቱ ራስ ላይ እጁን ይጫን፤ በመገናኛው ድንኳን ፊት ለፊት ይረደው፤ የአሮንም ልጆች ደሙን በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ይርጩት።

9 ከኅብረት መሥዋዕቱ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት የሚቀርብ ቊርባን አድርጎ ያምጣ፤ ሥቡን፣ እስከ ጀርባ ዐጥንቱ ድረስ የተቈረጠ ላቱን በሙሉ፣ የሆድ ዕቃውን የሸፈነውን ሥብ፣ ከሆድ ዕቃው ጋር የተያያዘውን ሥብ ሁሉ፣

10 ሁለቱን ኵላሊቶች፣ ኵላሊቶቹ ላይና በጐድኑ አጠገብ ያለውን ሥብ እንዲሁም የጒበቱን መሸፈኛ ከኵላሊቶቹ ጋር አብሮ አውጥቶ ያቅርብ።

11 ካህኑም ይህን ሁሉ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት የሚቀርብ የመብል ቊርባን አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያቃጥል።

12 “ ‘መሥዋዕቱ ፍየል ከሆነ፣ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያቅርብ፤

13 በራሱም ላይ እጁን ይጫንበት፤ በመገናኛው ድንኳን ፊት ለፊት ይረደው፤ የአሮንም ልጆች ደሙን በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ይርጩት።

14 ከሚያቀርበውም መሥዋዕት ላይ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት የሚቀርብ ቊርባን አድርጎ ያቅርብ፤ የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ሥብ፣ ከሆድ ዕቃው ጋር የተያያዘውን ሥብ ሁሉ፣