1 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
2 “ማንኛውም ሰው በዐደራ የተሰጠውን ወይም በመያዣነት የተቀበለውን በመካድና ባልንጀራውን በማጭበርበር ኀጢአት ቢሠራ፣ እግዚአብሔርንም (ያህዌ) ቢበድል ወይም ባልንጀራውን ቢቀማው ወይም ቢያታልለው፣
3 ወይም የጠፋ ነገር አግኝቶ አላየሁም ቢል ወይም በሐሰት ቢምል ወይም ሰዎች የሚያደርጉትን እንዲህ ያለውን ማናቸውንም ኀጢአት ቢሠራ፣
4 በዚህ ሁኔታ ኀጢአት ቢሠራና በደለኛ ቢሆን፣ የሰረቀውን ወይም የቀማውን ወይም በዐደራ የተሰጠውን ወይም ጠፍቶ ያገኘውን ይመልሳል፤
5 በሐሰት የማለበትንም ሁሉ ይመልስ፤ የበደል መሥዋዕቱን በሚያቀርብበት ጊዜ የወሰደውን በሙሉ የዋናውን አንድ አምስተኛ በመጨመር ለባለ ንብረቱ ይመልስ።
6 ከመንጋውም እንከን የሌለበትን ዋጋው ተመጣጣኝ የሆነ አውራ በግ ስለ በደሉ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ለማቅረብ ወደ ካህኑ ያምጣ፤