ዘኁልቍ 10:29-35 NASV

29 በዚህ ጊዜ ሙሴ የሚስቱን አባት የምድያማዊውን የራጉኤልን ልጅ ኦባብን፣ “እነሆ፤ እግዚአብሔር፣ (ያህዌ) ‘እሰጣችኋለሁ’ ወዳለን ምድር ጒዞ ጀምረናል፤ በመልካም ሁኔታ ስለምናኖርህ ከእኛ ጋር ሂድ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለእስራኤል በጎ ነገር ለማድረግ ቃል ገብቶአልና አለው።”

30 እርሱም መልሶ፣ “ይህስ አይሆንም፤ አልሄድም፤ ወደ አገሬና ወደ ወገኖቼ ተመልሼ እሄዳለሁ” አለው።

31 ሙሴ ግን እንዲህ አለ፤ “እባክህ አትለየን፤ በምድር በዳ ውስጥ የት መስፈር እንደሚገባን አንተ ታውቃለህ፤ ዐይናችንም ትሆናለህ።

32 ከእኛ ጋር ብትሄድ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከሚያደርግልን መልካም ነገር ሁሉ እኛም እናደርግልሃለን።”

33 ስለዚህ ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ተራራ ተነሥተው የሦስት ቀን መንገድ ተጓዙ፤ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቃል ኪዳን ታቦትም በእነዚያ ሦስት ቀናት ውስጥ የሚያርፉበትን ቦታ በመፈለግ ፊት ፊታቸው ይሄድ ነበር።

34 ከሰፈራቸው በሚነሡበት ጊዜ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ደመና ቀን ቀን ከላያቸው ነበር።

35 ታቦቱ ለጒዞ በተነሣ ጊዜ ሁሉ ሙሴ፣“እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፤ ተነሥ!ጠላቶችህ ይበተኑ፤የሚጠሉህም ከፊትህ ይሽሹ” ይል ነበር።