ዘኁልቍ

ምዕራፎች 3

መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ሌዋውያን

1 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን በሲና ተራራ ላይ ባነጋገረው ጊዜ የአሮንና የሙሴ ትውልድ ይህ ነበር፤ 2የአሮን ልጆች የበኵሩ ስም ናዳብ፣ የሌሎቹም አብዩድ አልዓዛርና ኢታምር ይባላል። 3እርሱ ለክህነት አገልግሎት የለያቸው፣ ካህናት ለመሆን የተቀቡት የአሮን ወንድ ልጆች ስም ይህ ነው፤ 4ናዳብና አብዩድ ግን በሲና ምድረ በዳ ባልተፈቀደ እሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕት ባቀረቡ ጊዜ እዚያው እፊቱ ወድቀው ሞቱ። ወንዶች ልጆች ስላልነበሯቸውም አልዓዛርና ኢታምር ብቻ አባታቸው አሮን በሕይወት በነበረበት ዘመን በክህነት ያገለግሉ ነበር። 5 እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ 6“የሌዊን ነገድ አምጥተህ ካህኑን አሮንን በአገልግሎቱ እንዲረዱት ከፊቱ አቁማቸው፤ 7በመገናኛው ድንኳን የማደሪያውን አገልግሎት በመፈጸም ለእርሱና ለማኅበረ ሰቡ ሁሉ የሚያስፈልጉትን ተግባሮች ያከናውኑ፤ 8የማደሪያውን ሥራ በመሥራትና የእስራኤላውያንን ግዴታ በመወጣት የመገናኛውን ድንኳን ሁሉ ይጠብቁ። 9ሌዋውያኑን ለአሮንና ለልጆቹ ስጥ፤ እነርሱም ከእስራኤላውያን ተለይተው ለእርሱ ፈጽመው የተሰጡ ናቸው። 10አሮንንና ልጆቹን ሹማቸው፤ እነርሱም ክህነታቸውን ይጠብቁ፤ ሌላ ሰው ማደሪያውን ቢቀርብ ግን ይገደል።” 11 እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ 12“እነሆ፤ በኵር ሆኖ በሚወለደው ሁሉ ምትክ ሌዋውያኑን ከእስራኤላውያን ወስጃለሁ፤ ስለዚህ ሌዋውያን የእኔ ናቸው፤ 13በኵር የሆነ ሁሉ የእኔ ነውና። በግብፅ ምድር በኵር የሆነውን ሁሉ በመታሁ ዕለት ከሰውም ሆነ ከእንስሳ ማናቸውንም የእስራኤልን በኵር ለራሴ ለይቻለሁ፤ የእኔ ይሁን። እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።” 14 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን በሲና ምድረ በዳ፣ 15“ሌዋውያንን በየቤታቸውና በየጐሣቸው ቍጠር፤ የምትቈጥረውም አንድ ወርና ከዚያ በላይ የሆነውን ወንድ ሁሉ ነው” አለው። 16ስለዚህ ሙሴ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ቃል በታዘዘው መሠረት እነዚህን ቈጠራቸው። 17የሌዊ ልጆች ስምጌድሶን፣ ቀዓትና ሜራሪ ነው። 18የጌድሶን ልጆች ጐሣ ስምሎቢኒና ሰሜኢ ነው። 19የቀዓት ጐሣዎች፤እንበረም፣ ይስዓር፣ ኬብሮን፣ ዑዝኤል። 20የሜራሪ ጐሣዎች፤ሞሖሊና ሙሲ።እንግዲህ የሌዋውያን ጐሣዎች በየቤተ ሰባቸው ሲቈጠሩ እነዚህ ናቸው። 21የሎቤናና የሰሜአ ጐሣዎች ከጌርሶን ወገን ናቸው፤ እነዚህ የጌርሶን ጐሣዎች ነበሩ። 22አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሆኖአቸው የተቈጠሩት ወንዶች በሙሉ ብዛታቸው ሰባት ሺህ አምስት መቶ ነበር። 23የጌርሶን ጐሣዎች በምዕራብ በኩል ከማደሪያው ድንኳን ጀርባ ይሰፍራሉ። 24የጌርሶን ጐሣዎች ቤተ ሰቦች አለቃ የዳኤል ልጅ ኤሊሳፍ ይሆናል። 25የጌድሶናውያን ኀላፊነት በመገናኛው ድንኳን ማደሪያውንና ድንኳኑን፣ መደረቢያዎቹን እንዲሁም በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ ያለውን መጋረጃ፣ 26የአደባባዩን መጋረጃዎች፣ ማደሪያ ድንኳኑንና መሠዊያውን የሚጋርደውን የአደባባዩን መግቢያ መጋረጃ፣ ገመዶቹንና ከነዚሁ ጋር ተያይዞ አገልግሎት የሚሰጠውን ሁሉ መጠበቅ ይሆናል። 27የእንበረማውያን፣ የይሰዓራውያን፣ የኬብሮናውያንና የዑዝኤላውያን ጐሣዎች ከቀዓት ወገን ናቸው፤ እነዚህ የቀዓት ጐሣዎች ነበሩ። 28አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሆኖአቸው የተቈጠሩት ወንዶች በሙሉ ብዛታቸው ስምንት ሺህ ስድስት መቶ ሲሆን፣ ቀዓታውያንም መቅደሱን የመጠበቅ ኀላፊነት ነበራቸው። 29የቀዓት ጐሣዎች ከማደሪያው ድንኳን በደቡብ በኩል ይሰፍራሉ። 30የቀዓት ጐሣዎች ቤተ ሰቦች አለቃ የዑዝኤል ልጅ ኤሊሳፈን ይሆናል። 31እነርሱም ታቦቱን፣ ጠረጴዛውን፣ መቅረዙን፣ መሠዊያዎቹን፣ ለመቅደሱ አገልግሎት የሚውሉትን ዕቃዎች፣ መጋረጃዎችንና ከነዚህ ጋር ተያይዞ አገልግሎት የሚሰጠውን ሁሉ ይጠብቃሉ። 32ዋናው የሌዋውያን አለቃ የካህኑ የአሮን ልጅ አልዓዛር ነው፤ እርሱም መቅደሱን ለመጠበቅ ኀላፊ በሆኑት ላይ ተሹሞ ነበር። 33የሞሖላውያንና የሙሳያውያን ጐሣዎች ከሜራሪ ወገን ናቸው፤ እነዚህም የሜራሪ ጐሣዎች ነበሩ። 34አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሆኖአቸው የተቈጠሩት ወንዶች ሁሉ ብዛታቸው ስድስት ሺህ ሁለት መቶ ነበር። 35የሜራሪም ጐሣዎች ቤተ ሰቦች አለቃ የአቢካኢል ልጅ ሱሪኤል ይሆናል፤ የሜራሪም ጐሣዎች ከማደሪያው ድንኳን በሰሜን በኩል ይሰፍራሉ። 36ሜራሪያውያንም የማደሪያውን ድንኳን ሳንቃዎች፣ መወርወሪያዎች፣ ምሰሶዎች፣ ምሰሶዎቹ የሚቆሙባቸውን እግሮች፣ የማደሪያ ዕቃዎችን ሁሉና ከነዚሁ ጋር ተያይዞ አገልግሎት የሚሰጠውን ሁሉ ለመጠበቅ ተሹመው ነበር። 37እንዲሁም የአደባባዩን ዙሪያ ምሰሶዎች ከነመቆሚያ እግሮቻቸው፣ ከነካስማቸውና ከነገመዶቻቸው ይጠብቃሉ። 38ሙሴ፣ አሮንና ልጆቹ ከማደሪያው ድንኳን በምሥራቅ በኩል በፀሓይ መውጫ ከመገናኛው ድንኳን ፊት ለፊት ይሰፍራሉ፤ እነርሱም እስራኤላውያንን ወክለው ማደሪያ ድንኳኑን ለመጠበቅ ኀላፊዎች ይሆናሉ፤ ወደ ማደሪያው ድንኳን የሚቀርብ ማንኛውም ሌላ ሰው ግን ይገደል። 39አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሆኖአቸው፣ ሙሴና አሮን በእግዚአብሔር ትእዛዝ በየጐሣቸው የቈጠሩአቸው የሌዋውያን ወንዶች ልጆች ጠቅላላ ብዛት ሃያ ሁለት ሺህ ነበር። 40 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በኵር ሆነው የተወለዱትን፣ አንድ ወርና ከዚያ በላይ የሆናቸውን እስራኤላውያን ወንዶች ሁሉ ቍጠር፤ ዝርዝራቸውንም ያዝ። 41በኵር በሆኑት በእስራኤላውያን ልጆች ሁሉ ምትክ ሌዋውያንን እንዲሁም በኵር በሆኑት በእስራኤላውያን ከብቶች ሁሉ ምትክ የሌዋውያንን ከብቶች ለእኔ አድርጋቸው፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።” 42ስለዚህ ሙሴ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት የእስራኤላውያንን በኵር ሁሉ ቈጠረ፤ 43አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሆኖአቸው በየስማቸው የተመዘገቡት ወንድ በኵሮች ሁሉ ብዛታቸው ሃያ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ሰባ ሦስት ነበር። 44ደግሞም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ 45“በእስራኤላውያን በኵሮች ምትክ ሌዋውያኑን፣ በከብቶቻቸውም ምትክ የሌዋውያኑን ከብቶች ውሰድ፤ ሌዋውያኑም የእኔ ይሁኑ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ። 46ቍጥራቸው ከሌዋውያን ቍጥር በሁለት መቶ ሰባ ሦስት በልጦ የተገኘውን እስራኤላውያን በኵሮች ለመዋጀት፣ 47ለእያንዳንዱ በኵር ክብደቱ ባለ ሃያ አቦሊ በሆነው በቤተ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ልክ አምስት አምስት ሰቅል ተቀበል፤ 48የተረፉትንም እስራኤላውያን ለመዋጀት ገንዘቡን ለአሮንና ለልጆቹ ስጥ።” 49ስለዚህ ሙሴ በሌዋውያኑ ተዋጅተው ቍጥራቸው ትርፍ ከሆነው በኵሮች ላይ የመዋጃውን ገንዘብ ተቀበለ፤ 50ከእስራኤላውያን በኵሮች ላይ በቤተ መቅደሱ ሰቅል ልክ አንድ ሺህ ሦስት መቶ ስልሳ አምስት ሰቅል ሰበሰበ። 51ሙሴም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ቃል በታዘዘው መሠረት የመዋጃውን ገንዘብ ለአሮንና ለልጆቹ ሰጣቸው።