ዘኁልቍ 8 NASV

የመብራቶቹ አቀማመጥ

1 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

2 “አሮንን ተናገረው፤ እንዲህም በለው፤ ‘ሰባቱን መብራቶች በየቦታቸው በምታስቀምጥበት ጊዜ በመቅረዙ ፊት ለፊት ላለው አካባቢ ብርሃን ይሰጣሉ።’ ”

3 አሮንም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን ባዘዘው መሠረት መብራቶቹ በመቅረዙ ላይ ሆነው ፊት ለፊት እንዲያበሩ አስቀመጣቸው።

4 የመቅረዙ አሠራር እንዲህ ነበር፤ ከመቆሚያው እስከ አበቦቹ ያለው ከተቀጠቀጠ ወርቅ የተሠራ ሲሆን፣ የመቅረዙም አሠራር እግዚአብሔር (ያህዌ) ለሙሴ ባሳየው መሠረት ነበር።

የሌዋውያን ለአገልግሎት መለየት

5 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

6 “ሌዋውያኑን ከእስራኤላውያን መካከል ለይተህ በሥርዐቱ መሠረት አንጻቸው።

7 ስታነጻቸውም እንዲህ አድርግ፤ በሚያነጻ ውሃ እርጫቸው፤ ገላቸውን በሙሉ ተላጭተው ልብሳቸውን ይጠቡ፤ በዚህም ይንጹ።

8 በዘይት ከተለወሰ ልም ዱቄት የእህል ቍርባን ጋር አንድ ወይፈን ይውሰዱ፤ ከዚያም ለኀጢአት መሥዋዕት የሚሆን ሌላ ወይፈን አንተ ትወስዳለህ።

9 ሌዋውያኑን ወደ መገናኛው ድንኳን ፊት አምጣ፤ መላውንም የእስራኤል ማኅብረ ሰብ ሰብስብ፤

10 ሌዋውያኑን በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት አቅርብ፤ ከዚያም እስራኤላውያን እጃቸውን ይጫኑባቸው።

11 ከዚያም አሮን ሌዋውያኑን የእግዚአብሔርን (ያህዌ) አገልግሎት ለማከናወን ዝግጁ እንዲሆኑ ከእስራኤላውያን መካከል እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያቅርባቸው።

12 “ሌዋውያኑ እጃቸውን በወይፈኖቹ ራስ ላይ ከጫኑ በኋላ ለሌዋውያኑ ማስተስረያ ይሆኑ ዘንድ የኀጢአት መሥዋዕት፣ ሌላውን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርባቸው።

13 ከዚያም ሌዋውያኑን በአሮንና በልጆቹ ፊት አቁማቸው፤ እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት አድርገህም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርባቸው።

14 በዚህ መሠረት ሌዋውያኑን ከእስራኤላውያን ትለያቸዋለህ፤ እነርሱም የእኔ ይሆናሉ።

15 “ሌዋውያኑን ካነጻሐቸውና እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት አድርገህ ካቀረብሀቸው በኋላ አገልግሎታቸውን ለመፈጸም ወደ መገናኛው ድንኳን ይመጣሉ፤

16 እነርሱም ሙሉ በሙሉ የእኔ እንዲሆኑ የተሰጡኝ እስራኤላውያን ናቸው፤ ከማንኛዪቱም እስራኤላዊት በተወለደ በኵር ወንድ ልጅ ምትክ የራሴ እንዲሆኑ ወስጃቸዋለሁ።

17 ከሰውም ሆነ ከእንስሳ በእስራኤል የተወለደ ማንኛውም በኵር ተባዕት የእኔ ነው፤ በግብፅ የነበረውን በኵር ሁሉ በመታሁ ጊዜ የእኔ እንዲሆኑ ለይቻቸዋለሁ።

18 በእስራኤል በተወለዱት ተባዕት በኵሮች ሁሉ ምትክም ሌዋውያኑን ወስጃለሁ።

19 እስራኤላውያንን ወክለው በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የሚፈጸመውን አገልግሎት እንዲያከናውኑና እስራኤላውያን ወደ ተቀደሰው ስፍራ ቢቀርቡ እንዳይቀሠፉ ያስተሰርዩላቸው ዘንድ፣ ከእስራኤላውያን ሁሉ መካከል ሌዋውያኑን ስጦታ አድርጌ ለአሮንና ለልጆቹ ሰጥቻቸዋለሁ።”

20 ሙሴና አሮን እንዲሁም የእስራኤል ማኅበረሰብ ሁሉ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን ባዘዘው መሠረት በሌዋውያኑ አደረጉ።

21 ሌዋውያኑ ራሳቸውን አነጹ፤ ልብሶቻቸውንም አጠቡ፤ ከዚያም አሮን እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት አቀረባቸው፤ እንዲነጹም ማስተስረያ አደረገላቸው።

22 ከዚህ በኋላ ሌዋውያኑ በአሮንና በልጆቹ ኀላፊነት ሥር ሆነው ድንኳን ውስጥ የሚፈጸመውን አገልግሎት ለማከናወን ገቡ። እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን ባዘዘው መሠረት አስፈላጊውን በሌዋውያኑ አደረጉ።

23 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

24 “ሌዋውያንን የሚመለከተው ደንብ ይህ ነው፤ በመገናኛው ድንኳን አገልግሎት ለመሳተፍ ሃያ አምስት ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸው ወንዶች ይመጣሉ፤

25 ዕድሜያቸው አምሳ ዓመት ሲሞላ ግን መደበኛ አገልግሎታቸውን ይተዉ፤ ዳግም ሥራ አይሥሩ።

26 ከዚያ በኋላ ወንድሞቻቸው በመገናኛው ድንኳን ሥራቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ ያግዟቸዋል እንጂ ራሳቸው መሥራት የለባቸውም። ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ የምታሰማራቸው በዚህ መልኩ ነው።”

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34 35 36