1 ከግብፅ ምድር በወጡ በሁለተኛው ዓመት፣ በመጀመሪያው ወር እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን በሲና ምድረ በዳ ተናገረው፤ እንዲህም አለው፤
2 “እስራኤላውያን በተወሰነው ጊዜ የፋሲካን በዓል እንዲያከብሩ አድርግ፤
3 በዓሉንም በዚህ ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን ፀሓይ በምትጠልቅበት ጊዜ በተወሰነው ሕግና ሥርዐት መሠረት ሁሉ አክብሩ።”
4 ስለዚህ ሙሴ ፋሲካን እንዲያከብሩ ለእስራኤላውያን ነገራቸው፤
5 እነርሱም በመጀመሪያው ወር፣ በዐሥራ አራተኛውም ቀን ፀሓይ በምትጠልቅበት ጊዜ በሲና ምድረ በዳ ፋሲካ አደረጉ፤ እስራኤላውያን እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን ባዘዘው መሠረት ሁሉንም አደረጉ።
6 አንዳንዶቹ ግን የሰው ሬሳ በመንካታቸው በሥርዐቱ መሠረት ረክሰው ስለ ነበር በዚያን ዕለት የፋሲካን በዓል ማክበር አልቻሉም፤ ስለዚህም በዚያኑ ዕለት ወደ ሙሴና ወደ አሮን መጥተው፣
7 ሙሴን፣ “በሬሳ ምክንያት ረክሰናል፤ ታዲያ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) መሥዋዕት ከሌሎቹ እስራኤላውያን ጋር ሆነን በተወሰነው ጊዜ እንዳናቀርብ ለምን እንከለከላለን?” አሉት።
8 ሙሴም፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ስለ እናንተ የሚያዘውን እስካውቅ ድረስ ጠብቁ” ሲል መለሰላቸው።
9 ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
10 “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘ከእናንተ ወይም ከዘሮቻችሁ ማንኛውም ሰው በሬሳ ምክንያት ቢረክስ ወይም ሩቅ መንገድ ቢሄድ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ፋሲካ ማክበር ይችላል፤
11 ይህንም በሁለተኛው ወር፣ በዐሥራ አራተኛው ቀን ፀሓይ በምትጠልቅበት ጊዜ ያክብሩ፤ የፋሲካውንም በግ እርሾ ከሌለበት ቂጣና ከመራራ ቅጠል ጋር ይብሉት።
12 እስኪነጋ ድረስ ከዚህ ምንም አያስተርፉ፤ ከዐጥንቱም ምንም አይስበሩ፤ ፋሲካን በሚያከብሩበት ጊዜ ሥርዐቱን በሙሉ መጠበቅ አለባቸው።
13 በሥርዐቱም መሠረት ንጹሕ የሆነ ወይም ሩቅ መንገድ ያልሄደ ሰው ፋሲካን ሳያከብር ቢቀር፣ ያ ሰው የእግዚአብሔርን (ያህዌ) መሥዋዕት በተወሰነው ጊዜ አላቀረበምና ከወገኖቹ ፈጽሞ ይለይ፤ ያም ሰው የኀጢአቱን ዋጋ ይቀበላል።
14 “ ‘በመካከላችሁ የሚኖር መጻተኛ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ፋሲካ ለማክበር ቢፈልግ በሕጉና በሥርዐቱ መሠረት መፈጸም አለበት፤ ለመጻተኛውም ሆነ ለአገሬው ተወላጅ የሚኖራችሁ ሕግ አንድ ይሁን።’ ”
15 ማደሪያው በተተከለ ዕለት ደመናው የምስክሩን ድንኳን ሸፈነው፤ ከምሽት እስከ ንጋት ድረስ ማደሪያውን የሸፈነው ደመና እሳት ይመስል ነበር።
16 ይህ በዚህ ሁኔታ ቀጠለ፤ ደመናው ማደሪያውን ሸፈነው፤ በሌሊትም የእሳት መልክ ነበረው።
17 ደመናው ከድንኳኑ ላይ በሚነሣበት ጊዜ እስራኤላውያን ጒዞአቸውን ይጀምሩ ነበር፤ ደመናው በሚቆምበት ቦታ ደግሞ ይሰፍሩ ነበር፤
18 እስራኤላውያን ጒዞ የሚጀምሩትም ሆነ የሚሰፍሩት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ትእዛዝ ነበር። ደመናው በድንኳኑ ላይ በሚቈይበት ጊዜ ሁሉ ከሰፈር አይንቀሳቀሱም ነበር።
19 ደመናው በድንኳኑ ላይ ብዙ ቀን ቢቈይም እስራኤላውያን የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ትእዛዝ ይጠብቃሉ እንጂ ተነሥተው አይጓዙም።
20 አንዳንድ ጊዜ ደመናው በድንኳኑ ላይ የሚቈየው ለጥቂት ቀን ብቻ ነበር፤ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ትእዛዝ ይሰፍራሉ፤ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ትእዛዝ ጒዞ ይጀምራሉ፤
21 አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ደመናው ከምሽት እስከ ንጋት ብቻ ይቈያል፤ ደመናው ንጋት ላይ ሲነሣም ጒዞአቸውን ይጀምራሉ፤ ቀንም ይሁን ሌሊት ደመናው ከተነሣ ጒዞ ይጀምራሉ።
22 ደመናው በድንኳኑ ላይ ለሁለት ቀንም ይሁን ለወር ወይም ለዓመት ቢቈይ፣ እስራኤላውያን በሰፈር ይቈያሉ እንጂ ጒዞአቸውን አይቀጥሉም።
23 በእግዚአብሔር (ያህዌ) ትእዛዝ ይሰፍራሉ፤ በእግዚአብሔርም (ያህዌ) ትእዛዝ ይጓዛሉ፤ እነርሱም በሙሴ አማካይነት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይጠብቁ ነበር።