1 እስራኤላውያን በየነገዳቸው ተከፋፍለው በሙሴና በአሮን መሪነት ከግብፅ ወጥተው፣ በጒዞ ላይ ሳሉ የሰፈሩባቸው ቦታዎች እነዚህ ናቸው፤
2 ሙሴም በጒዞአቸው ላይ ሳሉ የሰፈሩባቸውን ቦታዎች በእግዚአብሔር (ያህዌ) ትእዛዝ መዘገበ፤ በየቦታው እየሰፈሩ ያደረጉት ጒዞም ይህ ነው፤
3 እስራኤላውያን በመጀመሪያው ወር በዐሥራ አምስተኛውም ቀን በፋሲካ ማግስት ከራምሴ ተነሡ፤ ግብፃውያን ሁሉ እያዩአቸውም በልበ ሙሉነት ተጓዙ።
4 በዚህ ጊዜ ግብፃውያን እግዚአብሔር (ያህዌ) ከመካከላቸው የገደለባቸውን በኵሮቻቸውን ይቀብሩ ነበር፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) በግብፅ አማልክት ላይ ፈርዶ ነበር።
5 እስራኤላውያን ከራምሴ ተነሥተው በሱኮት ሰፈሩ።
6 ከሱኮትም ተነሥተው በምድረ በዳው ዳርቻ በምትገኘው በኤታም ሰፈሩ።
7 ከኤታም ተነሥተው ከበኣልዛፎን በስተ ምሥራቅ ወዳለችው ወደ ፊሀሒሮት በመመለስ በሚግዶል አጠገብ ሰፈሩ።
8 ከፊሀሒሮት ተነሥተው በባሕሩ ውስጥ በማለፍ ወደ ምድረ በዳው ሄዱ፤ ከዚያም በኤታም ምድረ በዳ ሦስት ቀን ተጒዘው በማራ ሰፈሩ።
9 ከማራ ተነሥተው ዐሥራ ሁለት የውሃ ምንጮችና ሰባ የተምር ዛፎች ወደነበሩበት ወደ ኤሊም መጥተው በዚያ ሰፈሩ።
10 ከኤሊም ተነሥተው በቀይ ባሕር አጠገብ ሰፈሩ።
11 ከቀይ ባሕር ተነሥተው በሲን ምድረ በዳ ሰፈሩ።
12 ከሲን ምድረ በዳ ተነሥተው በራፍቃ ሰፈሩ።
13 ከራፍቃ ተነሥተው በኤሉስ ሰፈሩ።
14 ከኤሉስ ተነሥተው በራፊዲም ሰፈሩ፤ በዚያም ሕዝቡ የሚጠጣው ውሃ አልበረም።
15 ከራፊዲም ተነሥተው በሲና ምድረ በዳ ሰፈሩ።
16 ከሲና ምድረ በዳ ተነሥተው በቂብሮት ሃታቫ ሰፈሩ።
17 ከቂብሮት ሃታቫ ተነሥተው በሐጼሮት ሰፈሩ።
18 ከሐጼሮት ተነሥተው በሪትማ ሰፈሩ።
19 ከሪትማ ተነሥተው በሬሞን ዘፋሬስ ሰፈሩ።
20 ከሬሞን ዘፋሬስ ተነሥተው በልብና ሰፈሩ።
21 ከልብና ተነሥተው በሪሳ ሰፈሩ።
22 ከሪሳ ተነሥተው በቀሄላታ ሰፈሩ።
23 ከቀሄላታ ተነሥተው በሻፍር ተራራ ሰፈሩ።
24 ከሻፍር ተራራ ተነሥተው በሐራዳ ሰፈሩ።
25 ከሐራዳ ተነሥተው በማቅሄሎት ሰፈሩ።
26 ከማቅሄሎት ተነሥተው በታሐት ሰፈሩ።
27 ከታሐት ተነሥተው በታራ ሰፈሩ።
28 ከታራ ተነሥተው በሚትቃ ሰፈሩ።
29 ከሚትቃ ተነሥተው በሐሽሞና ሰፈሩ።
30 ከሐሽሞና ተነሥተው በምሴሮት ሰፈሩ።
31 ከምሴሮት ተነስተው በብኔያዕቃን ሰፈሩ።
32 ከብኔያዕቃን ተነሥተው በሖርሃጊድጋድ ሰፈሩ።
33 ከሖርሃጊድጋድም ተነሥተው በዮጥባታ ሰፈሩ።
34 ከዮጥባታ ተነሥተው በዔብሮና ሰፈሩ።
35 ከዔብሮና ተነሥተው በዔጽዮንጋብር ሰፈሩ።
36 ከዔጽዮንጋብር ተነሥተው በጺን ምድረ በዳ ባለችው በቃዴስ ሰፈሩ።
37 ከቃዴስ ተነሥተው በኤዶም ዳርቻ ባለው በሖር ተራራ ሰፈሩ።
38 በእግዚአብሔር (ያህዌ) ትእዛዝ ካህኑ አሮን ወደ ሖር ተራራ ወጣ፤ እዚያም እስራኤላውያን ከግብፅ በወጡ በአርባኛው ዓመት፣ በአምስተኛው ወር፣ ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ሞተ።
39 አሮን በሖር ተራራ ላይ ሲሞት፣ ዕድሜው መቶ ሃያ ሦስት ዓመት ነበር።
40 በከነዓን በምትገኘው በኔጌብ የሚኖረው ከነዓናዊው የዓራድ ንጉሥ፣ የእስራኤላውያንን መምጣት ሰማ።
41 እነርሱም ከሖር ተራራ ተነሥተው በሴልሞና ሰፈሩ።
42 ከሴልሞና ተነሥተው በፋኖን ሰፈሩ።
43 ከፋኖን ተነሥተው በአቦት ሰፈሩ።
44 ከአቦት ተነሥተው በሞዓብ ዳርቻ በምትገኘው በኢየአባሪም ሰፈሩ።
45 ከኢይም ተነሥተው በዲቦንጋድ ሰፈሩ።
46 ከዲቦንጋድ ተነሥተው በዓልሞን ዲብላታይም ሰፈሩ።
47 ከዓልሞንዲብላታይም ተነሥተው በናባው አጠገብ በሚገኙት በዓብሪም ተራራዎች ላይ ሰፈሩ።
48 ከዓብሪም ተራራዎች ተነሥተው ከኢያሪኮ ማዶ በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ ባለው በሞዓብ ሜዳ ላይ ሰፈሩ።
49 እዚያም በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ በሞዓብ ሜዳ ከቤት የሺሞት እስከ አቤልስጢም ባለው ስፍራ ሰፈሩ።
50 ከኢያሪኮ ማዶ በዮርዳኖስ አጠገብ ባለው በሞዓብ ሜዳ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
51 “እስራኤላውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘ወደ ከነዓን ለመግባት ዮርዳኖስን ስትሻገሩ፣
52 የምድሪቱን ነዋሪዎች በሙሉ ከፊታችሁ አሳዳችሁ አስወጧቸው፤ የተቀረጹ ምስሎቻቸውንና ቀልጠው የተሠሩ ጣዖቶቻቸውን በሙሉ አጥፉ፤ እንዲሁም በኰረብታ ላይ የተሠሩትን መስገጃዎቻቸውን ሁሉ አፈራርሱ።
53 ምድሪቱን ርስት አድርጌ ሰጥቻችኋለሁና ውረሷት፤ ኑሩባትም።
54 ምድሪቱንም በየጐሣዎቻችሁ በዕጣ ተከፋፈሉ። ከፍ ያለ ቊጥር ላለው ሰፋ ያለውን፣ ዝቅተኛ ቊጥር ላለው ደግሞ አነስተኛውን ስጡ፤ ምንም ይሁን ምን በዕጣ የወጣላቸው፣ የየራሳቸው ርስት ይሆናል። አከፋፈሉም በየአባቶቻችሁ ነገዶች አንጻር ይሁን።
55 “ ‘የምድሪቱን ነዋሪዎች አሳዳችሁ ሳታስወጧቸው ብትቀሩ ግን፣ እንዲኖሩ የተዋችኋቸው ሰዎች ለዐይናችሁ ስንጥር፣ ለጐናችሁም እሾኽ ይሆኑባችኋል፤ በምትኖሩበትም ምድር ችግር ይፈጥሩባችኋል።
56 እኔም በእነርሱ ላይ ለማድረግ ያሰብሁትን በእናንተ ላይ አደርግባችኋለሁ።’ ”