1 በዚያች ሌሊት ማኅበረ ሰቡ ሁሉ ድምፁን ከፍ አድርጎ ጮኸና አለቀሰ።
2 እስራኤላውያን በሙሉ በሙሴና በአሮን ላይ አጒረመረሙ፤ ማኅበሩም ሁሉ እንዲህ አሉአቸው፤ “ምነው በግብፅ ወይም በዚህ ምድረ በዳ ሞተን ባረፍነው ኖሮ!
3 እግዚአብሔር (ያህዌ) ወደዚች ምድር የሚያመጣን ለምንድ ነው? በሰይፍ እንድንወድቅ ነውን? ሚስቶቻችንና ልጆቻችንም ይማረካሉ፤ ታዲያ ወደ ግብፅ መመለሱ አይሻለንም?”
4 እርስ በርሳቸውም፣ “አለቃ መርጠን ወደ ግብፅ እንመለስ” ተባባሉ።
5 ከዚያም ሙሴና አሮን እዚያ በተሰበሰቡት በመላው እስራኤላውያን ማኅበር ፊት በግንባራቸው ተደፉ።
6 ምድሪቱን ከሰለሏት መካከል የነበሩት የነዌ ልጅ ኢያሱና የዩፎኒ ልጅ ካሌብ ልብሳቸውን ቀደዱ፤
7 ለመላው የእስራኤል ማኅበርም እንዲህ አሉ፤ “ዞረን ያየናትና የሰለልናት ምድር እጅግ ሲበዛ መልካም ናት።
8 እግዚአብሔር (ያህዌ) በእኛ ደስ ከተሰኘብን ማርና ወተት ወደምታፈሰው ወደዚያች ምድር መርቶ ያገባናል፤ ለእኛም ይሰጠናል።
9 ብቻ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ላይ አታምፁ፤ እንደ እንጀራ እንጐርሳቸዋለንና የምድሪቱን ሰዎች አትፍሩአቸው። ጥላቸው ተገፎአል፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ከእኛ ጋር ነውና አትፍሯቸው።”
10 መላው ማኅበር ግን በድንጋይ ሊወግሯቸው ተነጋገሩ፤ ከዚያም የእግዚአብሔር (ያህዌ) ክብር በመገናኛው ድንኳን ለእስራኤላውያን ሁሉ ተገለጠ።
11 እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ይህ ሕዝብ እስከ መቼ ይንቀኛል” እነዚህን ሁሉ ታምራት በመካከሉ እያደረግሁ የማያምንብኝስ እስከ መቼ ነው?
12 በቸነፈር እመታዋለሁ፤ እደመስሰዋለሁም፤ አንተን ግን ብርቱና ታላቅ ለሆነ ሕዝብ አደርግሃለሁ።”
13 ሙሴ እግዚአብሔርን (ያህዌ) እንዲህ አለው፤ “ነገሩን ግብፃውያን ቢሰሙትስ! ይህን ሕዝብ በኀይልህ ከመካከላቸው አውጥተኸዋልና፤
14 የተደረገውንም በዚች ምድር ለሚኖሩት ሰዎች ይነግሯቸዋል። እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፣ አንተ ከዚህ ሕዝብ ጋር መሆንህን፣ ደግሞም አንተ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፤ ፊት ለፊት እንደታየህና ደመናህ በላያቸው እንደሆነ፣ አንተም ቀን በደመና ዐምድ ሌሊትም በእሳት ዐምድ እፊት እፊታቸው እየሄድህ እንደ መራሃቸው ቀድሞውኑ ሰምተዋል።
15 ታዲያ ይህን ሁሉ ሕዝብ በአንድ ጊዜ ብትፈጀው ዝናህን የሰሙ ሕዝቦች፣
16 ‘እግዚአብሔር (ያህዌ) ለዚህ ሕዝብ ይሰጠው ዘንድ በመሐላ ቃል ወደ ገባለት ምድር ሊያስገባው ባለመቻሉ በምድረ በዳ ፈጀው’ ይሉሃል።
17 “አሁንም እንዲህ ስትል በተናገርኸው መሠረት የጌታ ኀይል ይገለጥ፤
18 ‘እግዚአብሔር (ያህዌ) ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩ የበዛ፣ ኀጢአትንና ዐመፃን ይቅር የሚል፣ በደለኛውን ግን ሳይቀጣ የማይተው፣ ስለ አባቶቻቸውም ኀጢአት ልጆችን እስከ ሦስትና አራት ትውልድ የሚቀጣ ነው።’
19 ከግብፅ ከወጡበት ጊዜ አንሥቶ እስካሁን ድረስ ይቅር እንዳልሃቸው ሁሉ እንደ ፍቅርህ ታላቅነት መጠን እባክህ አሁንም የዚህን ሕዝብ ኀጢአት ይቅር በል።”
20 እግዚአብሔርም (ያህዌ) እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “በጠየቅኸው መሠረት ይቅር ብያቸዋለሁ፤
21 ይሁን እንጂ ሕያው እንደ መሆኔና የእግዚአብሔርም (ያህዌ) ክብር ምድርን ሁሉ የሞላ እንደ መሆኑ መጠን፣
22 ክብሬን ደግሞም በግብፅና በምድረ በዳ ያደረግኋቸውን ታምራት አይተው ካልታዘዙኝና ዐሥር ጊዜ ከተፈታተኑኝ ሰዎች አንዳቸውም፣
23 ለአባቶቻቸው እሰጣቸው ዘንድ በመሐላ ቃል የገባሁላቸውን ምድር አያዩዋትም። የናቀኝ ማንኛውም ሰው ፈጽሞ አያያትም፤
24 አገልጋዬ ካሌብ ግን የተለየ መንፈስ ስላለውና በፍጹም ልቡ የተከተለኝ በመሆኑ ሄዶባት ወደ ነበረችው ምድር አስገባዋለሁ፤ ዘሮቹም ይወርሷታል።
25 አማሌቃውያንና ከነዓናውያን በሸለቆው የሚኖሩ ስለ ሆነ በነገው ዕለት ተመልሳችሁ በቀይ ባሕር መንገድ ወደ ምድረ በዳው ሂዱ።”
26 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤
27 “ይህ ክፉ ማኅበረሰብ በእኔ ላይ የሚያጒረመርመው እስከ መቼ ነው? የእነዚህን ነጭናጮች እስራኤላውያን ማጒረምረም ሰምቻለሁ።
28 ስለዚህ እንዲህ በላቸው፤ ‘እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ ይላል፤ እኔ ሕያው ነኝ፤ ስትናገሩ የሰማኋችሁን እነዚያን ነገሮች አደርግባችኋለሁ፤
29 በተደረገው ቈጠራ መሠረት፣ ሃያ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ የሆናችሁና በእኔም ላይ ያጒረመረማችሁ ሁሉ በድናችሁ በዚህ ምድረ በዳ ይወድቃል።
30 መኖሪያችሁ እንድትሆን በጽኑ ወደ ማልሁላችሁ ምድር ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በስተቀር ከእናንተ አንዳችሁም አትገቡባትም።
31 ይማረካሉ ያላችኋቸውን ልጆቻችሁን ግን አገባቸዋለሁ፤ እናንተ የናቃችኋትን ምድር እነርሱ ይደሰቱባታል።
32 እናንተ ግን፣ በድናችሁ በዚሁ ምድረ በዳ ወድቆ ይቀራል።
33 ካለማመናችሁ የተነሣ ከእናንተ የመጨረሻው በድን እዚሁ ምድረ በዳ እስኪወድቅ ድረስ፣ ልጆቻችሁ መከራ እየበሉ አርባ ዓመት እረኞች ይሆናሉ።
34 ምድሪቱን ለመሰለል በቈያችሁበት አርባ ቀን ልክ እያንዳንዱ ዓመት እንደ አንድ ዕለት ተቈጥሮ ስለ ኀጢአታችሁ አርባ ዓመት መከራ ትቀበላላችሁ፤ ምን ያህል በእናንተ ላይ እንደ ተነሣሁም ታውቃላችሁ።
35 እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ይህን ተናግሬአለሁ፤ ደግሞም አንድ ሆኖ በተነሣብኝ በዚህ ክፉ ማኅበረሰብ ሁሉ ላይ እነዚህን ነገሮች አደርጋለሁ፤ መጨረሻቸው በዚሁ ምድረ በዳ ይሆናል፤ እዚሁም ይሞታሉ።’ ”
36 ከዚህ በኋላ ምድሪቱን እንዲሰልሉ ሙሴ ልኳቸው የነበሩትና ከዚያ ተመልሰው ስለ ምድሪቱ ክፉ ወሬ በማሠራጨት ማኅበረ ሰቡ በሙሉ እንዲያጒረመርሙበት ያደረጉ፣
37 ስለ ምድሪቱም ክፉ ወሬ በማሠራጨት ተጠያቂ የሆኑት እነዚሁ ሰዎች ተቀሥፈው በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ሞቱ።
38 ምድሪቱን እንዲሰልሉ ከተላኩት ሰዎች በሕይወት የተረፉት የነዌ ልጅ ኢያሱና የዩፎኒ ልጅ ካሌብ ብቻ ነበሩ።
39 ሙሴም ይህን ለእስራኤላውያን ሁሉ በነገራቸው ጊዜ ክፉኛ አዘኑ።
40 በማግሥቱም ጠዋት ማልደው ወደ ተራራማው አገር ወጡ፤ እንዲህም አሉ፣ “ኀጢአት ሠርተናልና እግዚአብሔር (ያህዌ) ተስፋ ወደ ሰጠን ስፍራ እንወጣለን”።
41 ሙሴ ግን እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ትእዛዝ ለምን ትጥሳላችሁ? ይህም አይሳካላችሁም!
42 እግዚአብሔር (ያህዌ) ከእናንተ ጋር ስላይደለ አትውጡ፤ በጠላቶቻችሁ ድል ትመታላችሁ፤
43 አማሌቃውያንና ከነዓናውያን በዚያ ያጋጥሟችኋልና። እግዚአብሔርን (ያህዌ) ስለተዋችሁትና እርሱም ከእናንተ ጋር ስለማይሆን በሰይፍ ትወድቃላችሁ።”
44 ሙሴም ሆነ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ታቦት ከሰፈር ሳይነሡ በስሜት ተገፋፍተው ብቻ ወደ ተራራማው አገር ወጡ።
45 በዚህ ጊዜ በተራራማው አገር የሚኖሩት አማሌቃውያንና ከነዓናውያን ወርደው ወጉአቸው፤ እስከ ሔርማ ድረስም አሳደዱአቸው።