1 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
2 “እስራኤላውያንን እዘዛቸው፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘ርስት አድርጋችሁ በዕጣ ወደምትካፈሏት ወደ ከነዓን ምድር በምትገቡበት ጊዜ አዋሳኞቿ እነዚህ ይሆናሉ፤
3 “ ‘የደቡብ ድንበራችሁ በኤዶም ወሰን ላይ ካለው ከጺን ምድረ በዳ ጥቂቱን ይጨምራል፤ በምሥራቅም በኩል የደቡብ ድንበራችሁ ከጨው ባሕር ጫፍ ይጀምርና
4 በአቅረቢም መተላለፊያ አቋርጦ እስከ ጺን ይሄድና በስተ ደቡብ እስከ ቃዴስ በርኔ ይዘልቃል፤ ከዚያም በሐጸር አዳር ዐልፎ እስከ ዓጽሞን ይደርስና
5 ዞሮ ከግብፅ ወንዝ ደረቅ መደብ ጋር በመገናኘት መጨረሻው ባሕሩ ይሆናል።
6 “ ‘የምዕራቡ ድንበራችሁ ደግሞ የታላቁ ባሕር ዳርቻ ይሆናል። በምዕራቡ በኩል ያለው ወሰናችሁም ይኸው ነው።
7 “ ‘የሰሜን ድንበራችሁን ከታላቁ ባሕር እስከ ሖር ተራራ ምልክት አድርጉበት፤
8 ከሖር ተራራ እስከ ሌቦ ሐማት እንደዚሁ አድርጉ፤ ከዚያም ወሰኑ እስከ ጽዳድ ይሄድና
9 እስከ ዚፍሮን በመቀጠል መጨረሻው ሐጻርዔናን ይሆናል፤ በሰሜን በኩል ያለው ወሰናችሁ ይኸው ነው።
10 “ ‘ለምሥራቁ ድንበራችሁም እንደዚሁ ከሐጸርዔናን እስከ ሴፋማ ምልክት አድርጉበት።
11 ወሰኑም ከሴፋማ አንሥቶ ከዓይን በስተ ምሥራቅ እስካለው እስከ ሪብላ ቊልቊል ይወርድና ከኪኔሬት ባሕርሀ በስተ ምሥራቅ እስካሉት ሸንተረሮች ድረስ ይዘልቃል።
12 ከዚያም ወሰኑ የዮርዳኖስን ወንዝ ተከትሎ መጨረሻው የጨው ባሕር ይሆናል።“ ‘እንግዲህ በዙሪያዋ ካሉት ወሰኖቿ ጋር ምድራችሁ ይህች ናት።’ ”
13 ሙሴ እስራኤላውያንን እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፤ “ይህችን ምድር ርስት አድርጋችሁ በዕጣ ደልድሉ፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ለዘጠኙና ለግማሹ ነገድ እንድትሰጥ አዞአል፤
14 የሮቤል ነገድ ቤተ ሰቦች፣ የጋድ ነገድ ቤተ ሰቦች እንዲሁም የምናሴ ነገድ እኩሌታ ርስታቸውን ተቀብለዋልና።
15 እነዚህ ሁለቱ ነገዶችና እኩሌታው ነገድ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ፣ ከኢያሪኮ ማዶ በፀሓይ መውጫ በኩል ርስታቸውን ተቀብለዋል።”
16 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
17 “ምድሪቱን ርስት አድርገው የሚያከፋፍሏችሁ ካህኑ አልዓዛርና የነዌ ልጅ ኢያሱ ናቸው፤
18 ምድሪቱን በማከፋፈሉ እንዲረዱም ከየነገዱ አንዳንድ መሪ ውሰዱ።
19 ስማቸውም ይህ ነው፤ከይሁዳ ነገድ፣ የዮፎኒ ልጅ ካሌብ፤
20 ከስምዖን ነገድ፣የዓሚሁድ ልጅ ሰላሚኤል፤
21 ከብንያም ነገድ፣የኪስሎን ልጅ ኤልዳድ፤
22 የዳን ነገድ መሪ፣የዩግሊ ልጅ ቡቂ፤
23 የዮሴፍ ልጅ የምናሴ ነገድ መሪ፣የሱፊድ ልጅ አኒኤል፤
24 የዮሴፍ ልጅ የኤፍሬም ነገድ መሪ፣የሺፍጣን ልጅ ቀሙኤል፤
25 የዛብሎን ነገድ መሪ፣የፈርናክ ልጅ ኤሊሳፈን፤
26 የይሳኮር ነገድ መሪ፣የሖዛ ልጅ ፈልጢኤል፤
27 የአሴር ነገድ መሪ፣የሴሌሚ ልጅ አሒሁድ፤
28 የንፍታሌም ነገድ መሪ፣የዓሚሁድ ልጅ ፈዳሄል።”
29 እነዚህ በከነዓን ምድር ለእስራኤላውያን ርስት እንዲያከፋፍሉ እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዛቸው ሰዎች ናቸው።