ዘኁልቍ 11:19-25 NASV

19 የምትበሉትም ለአንድ ወይም ለሁለት ቀን ወይም ለአምስት፣ ለዐሥር ወይም ለሃያ ቀን አይደለም፤

20 ነገር ግን በአፍንጫችሁ እስኪወጣና እስኪያንገፈግፋችሁ ድረስ ወር ሙሉ ትበሉታላችሁ፤ በመካከላችሁ ያለውን እግዚአብሔርን (ያህዌ) ንቃችሁ በፊቱ፣ “ለምን ከግብፅ ወጣን?” ብላችሁ አልቅሳችኋልና።’ ”

21 ሙሴ ግን እንዲህ አለ፤ “እነሆ እኔ በስድስት መቶ ሺህ እግረኛ መካከል እገኛለሁ፤ አንተ ደግሞ ‘ወር ሙሉ የሚበሉትን ሥጋ እኔ እሰጣቸዋለሁ’ ብለሃል፤

22 ታዲያ ስንት የበግ፣ የፍየልና የከብት መንጋ ቢታረድላቸው ይበቃ ይሆን? በባሕር ያለው ዓሣ ሁሉ ቢያዝ ሊዳረሳቸው ይችላልን?”

23 እግዚአብሔርም (ያህዌ) ለሙሴ፣ “በውኑ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ክንድ ይህን ያህል አጭር ነውን? የነገርሁህ ቃል እውነት መሆን አለመሆኑን አሁኑኑ ታየዋለህ” ሲል መለሰለት።

24 ሙሴም ወጣና እግዚአብሔር (ያህዌ) ያለውን ለሕዝቡ ነገራቸው፤ ከሕዝቡም ሽማግሌዎች ሰባውን ሰብስቦ በድንኳኑ ዙሪያ እንዲቆሙ አደረጋቸው።

25 ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) በደመና ወርዶ ተናገረው፤ በሙሴ ላይ ከነበረውም መንፈስ ወስዶ በሰባው ሽማግሌዎች ላይ አሳደረባቸው፤ መንፈሱ ባደረባቸውም ጊዜ ትንቢት ተናገሩ፤ ከዚያ በኋላ ግን አልደገሙትም።