4 ድብልቁ ሕዝብ ሌላ ምግብ ጐመጀ፤ እስራኤላውያንም እንዲህ እያሉ ያጒረመርሙ ጀመር፤ “ምነው የምንበላው ሥጋ ባገኘን ኖሮ!
5 በግብፅ ያለ ምንም ዋጋ የበላ ነው ዓሣ እንዲሁም ዱባው፣ በጢኹ፣ ኵራቱ፣ ነጭ ሽንኩርቱ ትዝ ይለናል።
6 አሁን ግን የምግብ ፍላጎታችን ጠፍቶአል፤ ከዚህ መና በስተቀር የምናየው የለም!”
7 መናው እንደ ድንብላል ዘር ትንንሽ ሆኖ የሙጫ መልክ ነበረው።
8 ሕዝቡ ተዘዋውሮ በመልቀም በወፍጮ ከፈጨ ወይም በሙቀጫ ከወቀጠ በኋላ በምንቸት ይቀቅለው ወይም ይጋግረው ነበር፤ ጣዕሙም በወይራ ዘይት የተጋገረ ያህል ይጣፍጥ ነበር።
9 ጤዛው ሌሊት በሰፈር ላይ በሚወርድበት ጊዜ መናውም እንዲሁ ይወርድ ነበር።
10 ሙሴ፣ ሕዝቡ ሁሉ በየቤተ ሰቡ፣ በየድንኳኑ ደጃፍ ሆኖ ሲያለቅስ ሰማ። እግዚአብሔርም (ያህዌ) እጅግ ተቈጣ፤ ሙሴም ተጨነቀ።