ዘኁልቍ 16:12-18 NASV

12 ከዚያም ሙሴ የኤልያብን ልጆች ዳታንና አቤሮንን አስጠራቸው፤ እነርሱ ግን እንዲህ አሉ፤ “እኛ አንመጣም!

13 በምድረ በዳ ልትገድለን ማርና ወተት ከምታፈሰው ምድር ያወጣኸን አይበቃህም? አሁን ደግሞ በእኛ ላይ ጌታ መሆን ያምርሃል?

14 ከዚህም በቀር አንተ ማርና ወተት ወደምታፈሰው ምድር አላመጣኸንም፤ ወይም ዕርሻዎችንና የወይን ተክል ቦታዎች አላወረስከንም። ታዲያ የእነዚህን ሰዎች ዐይን ታወጣለህን? በጭራሽ አንመጣም!”

15 ሙሴም በጣም ተቈጣ፤ እግዚአብሔርንም (ያህዌ) “ቊርባናቸውን አትቀበል፤ እኔ ከእነዚህ ሰዎች የወሰድኩት አንድ አህያ እንኳ የለም፤ አንዳቸውንም አልበደልሁም” አለ።

16 ሙሴም ቆሬን እንዲህ አለው፤ “አንተና ተከታዮችህ እንዲሁም አሮን ነገ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ትቀርባላችሁ።

17 እያንዳንዱም ሰው ጥናውን ይወስዳል፤ ባጠቃላይ ሁለት መቶ አምሳ ጥናዎች ይሆናሉ፤ በዚያም ላይ ዕጣን ጨምሮ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያቀርባል፤ አንተና አሮንም ጥናዎቻችሁን እንደዚሁ ታቀርባላችሁ።

18 እያንዳንዱ ሰው ጥናውን በመያዝ ፍም አድርጎበት፣ ዕጣን ጨምሮበት ከሙሴና ከአሮን ጋር በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ቆመ።