32 አፏንም ከፍታ ሰዎቹን ከነቤተ ሰቦቻቸው እንዲሁም የቆሬን ሰዎች በሙሉ፣ ንብረታቸውንም ሁሉ ዋጠች።
33 እነርሱም ካላቸው ከማናቸውም ነገር ጋር ከነሕይወታቸው ወደ መቃብር ወረዱ፤ ምድሪቱም በላያቸው ተከደነችባቸው፤ ጠፉ፤ ከማኅበረ ሰቡም ተወገዱ።
34 ከጩኸታቸውም የተነሣ በአካባቢያቸው የነበሩት እስራኤላውያን ሁሉ፣ “ምድሪቱ እኛንም እኮ ልትውጠን ነው” ብለው ሸሹ።
35 እሳትም ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘንድ ወርዳ የሚያጥኑትን ሁለት መቶ አምሳ ሰዎች በላቻቸው።
36 እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
37 “ጥናዎቹ የተቀደሱ ናቸውና ከተቃጠሉት ሰዎች ዘንድ ወስደህ በውስጣቸው ያለውን ፍም አርቆ እንዲደፋ ለካህኑ ለአሮን ልጅ ለአልዓዛር ንገረው፤
38 እነዚህም ሕይወታቸውን ለማጥፋት ኀጢአት የሠሩ ሰዎች ጥና ናቸው፤ ጥናዎቹም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት የቀረቡና የተቀደሱ በመሆናቸው ለመሠዊያው መለበጫ እንዲሆኑ ቀጥቅጠህ አሣሣቸው፤ እነዚህም ለእስራኤላውያን ማስጠንቀቂያ ይሁኑ።”