ዘኁልቍ 16:5-11 NASV

5 ቆሬንና ተከታዮቹን በሙሉ እንዲህ አላቸው፤ “የእርሱ የሆነውና የተቀደሰው ማን መሆኑን እግዚአብሔር (ያህዌ) ነገ ጠዋት ይለያል፤ ወደ ራሱም ያመጣዋል፤ የሚመርጠውን ሰው ወደ ራሱ እንዲቀርብ ያደርገዋል።

6 ቆሬ፣ አንተና ተከታዮችህ ሁሉ እንዲህ አድርጉ፤ ጥናዎችን ውሰዱ፤

7 በማግስቱም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት እሳትና ዕጣን ጨምሩባቸው፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚመርጠውም ያ ሰው ቅዱስ ይሆናል፤ እናንት የሌዊ ልጆች፤ ከልክ ያለፋችሁትስ እናንተ ናችሁ።”

8 ደግሞም ሙሴ ቆሬን እንዲህ አለው፤ “እናንት ሌዋውያን አድምጡ

9 የእስራኤል አምላክ (ኤሎሂም) እናንተን ከቀሩት እስራኤላውያን ማኅበረሰብ መለየቱና በእግዚአብሔር (ያህዌ) ማደሪያ አገልግሎት እንድትፈጽሙ ወደ ራሱ ማቅረቡ፣ እንድታገለግሏቸውም በማኅበረ ሰቡ ፊት እንድትቆሙ ማድረጉ አይበቃችሁምን?

10 አንተንና ከአንተም ጋር ወገኖችህ የሆኑትን ሌዋውያንን ሁሉ ወደ ራሱ አቅርቧችኋል፤ እናንተ ግን የክህነቱንም ሥራ ደርባችሁ ለመያዝ ይኸው ትሯሯጣላችሁ።

11 አንተና ተከታዮችህ ሁሉ አባሪ ተባባሪ ሆናችሁ የተነሣችሁት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ላይ ነው፤ ለመሆኑ ታጒረመርሙበት ዘንድ አሮን ማነው?”