3 ለያንዳንዱ የነገድ አለቃ አንዳንድ በትር መኖር ስላለበት በሌዊ በትር ላይ የአሮንን ስም ጻፍ።
4 በትሮቹንም እኔ ከአንተ ጋር በምገናኝበት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ከምስክሩ ፊት ለፊት አስቀምጣቸው።
5 እኔ የምመርጠው ሰው በትርም ታቈጠቍጣለች፤ እስራኤላውያን በእናንተ ላይ ነጋ ጠባ የሚያደርጉትንም ማጒረምረም በዚህ እገታለሁ።
6 ሙሴም ለእስራኤላውያን ተናገራቸው፤ አለቆቻቸውም በቀደሙት በያንዳንዱ አባቶች ስም ዐሥራ ሁለት በትር ሰጡት፤ የአሮን በትርም በበትሮቹ መካከል ነበረች።
7 ሙሴም በትሮቹን ወስዶ በምስክሩ ድንኳን ውስጥ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት አኖራቸው።
8 በማግስቱ ሙሴ ወደ ምስክሩ ድንኳን ሲገባ በሌዊ ቤት ስም የቀረበችው የአሮን በትር ማቈጥቈጥ ብቻ ሳይሆን እንቡጥ አውጥታ፣ አብባና ለውዝ አፍርታ አገኛት።
9 ከዚያም ሙሴ በትሮቹን ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት አውጥቶ ወደ እስራኤላውያን ሁሉ አመጣቸው፤ እነርሱም አዩ፤ እያንዳንዱም ሰው የየራሱን በትር ወሰደ።