ዘኁልቍ 18:22-28 NASV

22 አድራጎቱ ኀጢአት ስለ ሆነ ሞት እንዳ ያስከትልባቸው ከእንግዲህ ወዲያ እስራኤላውያን ወደ መገናኛው ድንኳን አይጠጉ።

23 በመገናኛው ድንኳን የሚከናወነውን ሥራ የሚሠሩት ሌዋውያን ናቸው፤ በዚያም ለሚፈጸመው በደል ኀላፊነቱን ይሸከማሉ። ይህም ለሚመጡት ትውልዶች የዘላለም ሥርዐት ነው፤ ሌዋውያን በእስራኤላውያን መካከል ርስት አይሰጣቸውም።

24 በዚህ ፈንታም እስራኤላውያን መባ አድርገው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚያቀርቡትን ዐሥራት ለሌዋውያን ርስት አድርጌ ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔም እነርሱን በተመለከተ፣ ‘በእስራኤላውያን መካከል ርስት አይኖራቸውም’ ያልኩት በዚሁ ምክንያት ነው።”

25 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

26 “ሌዋውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘ርስት አድርጌ የምሰጣችሁን ዐሥራት ከእስራኤላውያን በምትቀበሉበት ጊዜ፣ እናንተም ካገኛችሁት ላይ አንድ ዐሥርኛ በማውጣት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መባ አድጋችሁ ታቀርባላችሁ።

27 ቊርባናችሁም ከዐውድማ እንደ ገባ እህል ወይም ከመጭመቂያ እንደ ወጣ ወይን ሆኖ ይቈጠርላችኋል።

28 እናንተም ከእስራኤላውያን ላይ ከምትቀበሉት ዐሥራት ሁሉ በዚሁ ዐይነት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መባ ታቀርባላችሁ፤ ከዚሁም የእግዚአብሔር (ያህዌ) ድርሻ የሆነውን ዐሥራት ለካህኑ ለአሮን ትሰጣላችሁ።