1 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤
2 “እስራኤላውያን ከምስክሩ ድንኳን ትይዩ ዙሪያውን ጥቂት ራቅ ብለው እያንዳንዱ ሰው በየዐርማውና በየቤተ ሰቡ ምልክት ሥር ይስፈር።”
3 “በምሥራቅ በኩል በፀሓይ መውጫ የይሁዳ ምድብ በየሰራዊቱና በዐርማቸው ሥር ይስፈር፤ የይሁዳ ሕዝብ አለቃ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን ነው፤
4 የሰራዊቱም ብዛት ሰባ አራት ሺህ ስድስት መቶ ነው።
5 “ከእነዚህ ቀጥሎ የይሳኮር ነገድ ይሰፍራል፤ የይሳኮር ሕዝብ አለቃ የሶገር ልጅ ናትናኤል ሲሆን፣
6 የሰራዊቱም ብዛት አምሳ አራት ሺህ አራት መቶ ነው።