1 በመጀመሪያው ወር መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ወደ ጺን ምድረ በዳ መጥተው በቃዴስ ተቀመጡ፤ እዚያ ማርያም ሞተች፤ ተቀበረችም።
2 በዚህ ጊዜ ለማኅበረ ሰቡ የሚሆን ውሃ አልነበረም፤ ሕዝቡም ሙሴንና አሮንን በመቃወም ተሰበሰቡ።
3 ሙሴን ተጣሉት፤ እንዲህም አሉት፤ “ወንድሞቻችን በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት በሞቱ ጊዜ ምነው እኛም ያኔ ሞተን ባረፍነው ኖሮ!
4 የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ማኅበረሰብ ወደዚህ ምድረ በዳ ያመጣችሁት ለምንድ ነው! ከነከብቶቻችን እዚሁ እንድናልቅ ነውን?
5 ከግብፅ አውጥታችሁ እህል ወይም በለስ፣ ወይን ወይም ሮማን ወደሌለበት ወደዚህ ክፉ ቦታ ያመጣችሁንስ ለምንድ ነው? የሚጠጣ ውሃ እንኳ ይታጣ!”