ዘኁልቍ 22:18-24 NASV

18 በለዓም ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “ሌላው ይቅርና ባላቅ በብርና በወርቅ የተሞላ ቤተ መንግሥቱን ቢሰጠኝ እንኳ፣ የአምላኬን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዝ በመጣስ ከዚያ ያለፈ ወይም ያነሰ ማንኛውንም ነገር ማድረግ አልችልም።

19 አሁንም ሌሎቹ እንዳደረጉት ሁሉ፣ እናንተም ዛሬ እዚሁ ዕደሩና እግዚአብሔር (ያህዌ) ምን እንደሚለኝ ደግሞ ልወቅ።”

20 በዚያች ሌሊት እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ወደ በለዓም መጥቶ፣ “እነዚህ ሰዎች የመጡት እንድትሄድላቸው እስከ ሆነ ድረስ አብረሃቸው ሂድ፤ ነገር ግን እኔ የምነግርህን ብቻ አድርግ።”

21 በለዓም በጠዋት ተነሣ፤ አህያውንም ጭኖ ከሞዓብ አለቆች ጋር ሄደ።

22 ይሁን እንጂ በለዓም በሄደ ጊዜ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በጣም ተቈጥቶ ስለ ነበር የእግዚአብሔር (ያህዌ) መልአክ ሊቃወመው በመንገዱ ላይ ቆመ። በለዓምም በአህያው ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ሁለት አሽከሮቹም አብረው ነበሩ።

23 አህያዪቱም የእግዚአብሔር (ያህዌ) መልአክ የተመዘዘ ሰይፍ ይዞ በመንገድ ላይ መቆሙን ባየች ጊዜ ከመንገድ ወጥታ ዕርሻ ውስጥ ገባች፤ በለዓምም ወደ መንገዱ እንድትመለስ መታት።

24 ከዚያም የእግዚአብሔር (ያህዌ) መልአክ በሁለቱም በኩል ግንብ ባለበት በሁለት የወይን ተክል ቦታ መካከል በሚገኝ ጠባብ መተላለፊያ ላይ ቆመ።