ዘኁልቍ 22:25-31 NASV

25 አህያዪቱም የእግዚአብሔርን (ያህዌ) መልአክ ባየች ጊዜ ወደ ግንቡ ተጠግታ የበለዓምን እግር አጣበቀችው፤ ስለዚህም እንደ ገና መታት።

26 የእግዚአብሔርም (ያህዌ) መልአክ ወደ ፊት ሄድ ብሎ ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ መተላለፊያ በሌለበት ጠባብ ቦታ ላይ ቆመ።

27 አህያዪቱም የእግዚአብሔርን (ያህዌ) መልአክ ባየች ጊዜ ከበለዓም በታች ተኛች፤ በለዓም ተቈጥቶ ነበርና በበትሩ ደበደባት።

28 ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) የአህያዪቱን አፍ ከፈተ፤ በለዓምንም፣ “እንዲህ አድርገህ ሦስት ጊዜ የመታኸኝ ምን አድርጌህ ነው?” አለችው።

29 በለዓምም መልሶ አህያዪቱን፣ “ስላላገጥሽብኝ ነዋ! በእጄ ሰይፍ ይዤ ቢሆን ኖሮ አሁኑኑ በገደልሁሽ ነበር” አላት።

30 አህያዪቱም ደግሞ በለዓምን እንዲህ አለችው፣ “ከብዙ ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የተቀመጥክብኝ አህያህ አይደለሁምን? ታዲያ ይህን የመሰለ ነገር የማድረግ ልማድ ነበረኝ?”እርሱም፣ “በጭራሽ!” አላት።

31 በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር (ያህዌ) የበለዓምን ዐይን ከፈተ፤ እርሱም የእግዚአብሔር (ያህዌ) መልአክ የተመዘዘ ሰይፍ እንደ ያዘ መንገዱ ላይ ቆሞ አየ፤ ጐንበስ ብሎም በግንባሩ ተደፋ።