ዘኁልቍ 22:3-9 NASV

3 ሞዓብም ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ ተሸበረ፤ በእርግጥም ሞዓብ በእስራኤላውያን ምክንያት በፍርሀት ተውጦ ነበር።

4 ሞዓባውያንም የምድያምን ሽማግሌዎች፣ “በሬ የመስክ ሣር ጠራርጎ እንደሚበላ ሁሉ፣ ይህም ሰራዊት በዙሪያችን ያለውን ሁሉ ጠራርጎ የሚያጠፋ ነው” አሏቸው።ስለዚህ በዚያን ጊዜ የሞዓብ ንጉሥ የነበረው የሴፎር ልጅ ባላቅ፣

5 ከወንዙ ዳር ባለች በትውልድ አገሩ በምትገኝ በፋቱራ የነበረውን የቢዖርን ልጅ በለዓምን እንዲጠሩት መልእክተኞች ላከ፤ እንዲህም አለ፤እነሆ ከብዛቱ የተነሣ ምድሩን የሸፈነ ሕዝብ ከግብፅ ወጥቶ በአቅራቢያዬ ሰፍሮአል።

6 ስለዚህ ይህን ሕዝብ መቋቋም ስለማልችል መጥተህ ርገምልኝ፤ ምናልባትም ድል አድርጌ ከአገሪቱ ላስወጣቸው የምችለው ከዚያ በኋላ ሊሆን ይችላል፤ አንተ የምትባርከው ቡሩክ፣ የምትረግመውም ርጉም እንደሚሆን ዐውቃለሁና።”

7 የሞዓብና የምድያም ሽማግሌዎችም ለሟርት የሚከፈለውን ዋጋ ይዘው ሄዱ፤ በለዓም ዘንድ በደረሱ ጊዜም የባላቅን መልእክት ነገሩት።

8 በለዓምም፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚሰጠኝን መልስ አመጣላችኋለሁና የዛሬን ሌሊት እዚሁ ዕደሩ” አላቸው። ስለዚህም የሞዓብ አለቆች ከእርሱ ዘንድ ቈዩ።

9 እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ወደ በለዓም መጥቶ፣ “ከአንተ ጋር ያሉት እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው?” ሲል ጠየቀው።