1 በለዓምም እግዚአብሔር (ያህዌ) እስራኤልን መባረክ እንደ ወደደ ባየ ጊዜ፣ እንደ ሌላው ጊዜ ሁሉ አስማት ለመሻት አልሄደም፤ ነገር ግን ፊቱን ወደ ምድረ በዳ መለሰ።
2 በለዓም አሻግሮ ተመልክቶ እስራኤል በየነገድ በየነገዱ ሆኖ መስፈሩን ሲያይ የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) መንፈስ በላዩ መጣበት፤
3 ንግሩንም እንዲህ ሲል ጀመረ፤“የዚያ ዐይኑ የተከፈተለት፣የቢዖር ልጅ የበለዓም ንግር፣
4 የዚያ የአምላክን (ኤሎሂም) ቃል የሚሰማ፣ሁሉን የሚችል የአምላክን ራእይ የሚያይ፣ከመሬት የተደፋው ዐይኖቹም የተከፈቱለት ሰው ንግር፤
5 “ያዕቆብ ሆይ፤ ድንኳኖችህ፣እስራኤል ሆይ፤ ማደሪያዎችህ እንዴት ያማሩ ናቸው!
6 “እንደ ሸለቆዎች፣በወንዝ ዳር እንዳሉም የአትክልት ስፍራዎች ተዘርግተዋል፤ በእግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ተተከሉ ሬቶች፣በውሃም አጠገብ እንዳሉ ዝግባዎች ናቸው።
7 ከማድጋቸው ውሃ ይፈሳል፤ዘራቸውም የተትረፈረፈ ውሃ ያገኛል፤“ንጉሣቸው ከአጋግ ይልቃል፤መንግሥታቸውም ከፍ ከፍ ይላል፤