1 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
2 “ይህን ትእዛዝ ለእስራኤላውያን ስጣቸው፤ ‘ሽታው ደስ እንዲያሰኘኝ በእሳት የሚቀርብልኝን የምግብ ቊርባን የተወሰነውን ጊዜ ጠብቃችሁ አቅርቡልኝ’ በላቸው።
3 ደግሞም እንዲህ በላቸው፤ ‘በእሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የምታቀርቡት መሥዋዕት ይህ ነው፤ አንድ ዓመት የሆናቸውንና እንከን የሌለባቸውን ሁለት ተባዕት የበግ ጠቦቶች መደበኛ የሚቃጠል መሥዋዕት በማድረግ በየዕለቱ አቅርቡ።
4 አንዱን ጠቦት ጠዋት ሌላውን ደግሞ ማታ አቅርቡ፤
5 ከዚህም ጋር ተወቅጦ በተጠለለ በሂን አንድ አራተኛ የወይራ ዘይት የተለወሰ የኢፍ አንድ ዐሥረኛ ልም ዱቄት የእህል ቊርባን አዘጋጁ።
6 ይህም ሽታው ደስ እንዲያሰኝ በእሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚቀርብ ምሥዋዕት ሲሆን፣ በሲና ተራራ የተደነገገ መደበኛ የሚቃጠል መሥዋዕት ነው።
7 ከእያንዳንዱ ጠቦት ጋር አብሮት የሚቀርበውም የመጠጥ ቊርባን ፈልቶ የወጣለት የሂን አንድ አራተኛ መጠጥ ይሆናል፤ የመጠጡንም ቊርባን በተቀደሰው ቦታ ላይ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አፍስሱት።