ዘኁልቍ
ምዕራፎች 3:22-28
መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም
22አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሆኖአቸው የተቈጠሩት ወንዶች በሙሉ ብዛታቸው ሰባት ሺህ አምስት መቶ ነበር።
23የጌርሶን ጐሣዎች በምዕራብ በኩል ከማደሪያው ድንኳን ጀርባ ይሰፍራሉ።
24የጌርሶን ጐሣዎች ቤተ ሰቦች አለቃ የዳኤል ልጅ ኤሊሳፍ ይሆናል።
25የጌድሶናውያን ኀላፊነት በመገናኛው ድንኳን ማደሪያውንና ድንኳኑን፣ መደረቢያዎቹን እንዲሁም በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ ያለውን መጋረጃ፣
26የአደባባዩን መጋረጃዎች፣ ማደሪያ ድንኳኑንና መሠዊያውን የሚጋርደውን የአደባባዩን መግቢያ መጋረጃ፣ ገመዶቹንና ከነዚሁ ጋር ተያይዞ አገልግሎት የሚሰጠውን ሁሉ መጠበቅ ይሆናል።
27የእንበረማውያን፣ የይሰዓራውያን፣ የኬብሮናውያንና የዑዝኤላውያን ጐሣዎች ከቀዓት ወገን ናቸው፤ እነዚህ የቀዓት ጐሣዎች ነበሩ።
28አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሆኖአቸው የተቈጠሩት ወንዶች በሙሉ ብዛታቸው ስምንት ሺህ ስድስት መቶ ሲሆን፣ ቀዓታውያንም መቅደሱን የመጠበቅ ኀላፊነት ነበራቸው።