1 እስራኤላውያን በየነገዳቸው ተከፋፍለው በሙሴና በአሮን መሪነት ከግብፅ ወጥተው፣ በጒዞ ላይ ሳሉ የሰፈሩባቸው ቦታዎች እነዚህ ናቸው፤
2 ሙሴም በጒዞአቸው ላይ ሳሉ የሰፈሩባቸውን ቦታዎች በእግዚአብሔር (ያህዌ) ትእዛዝ መዘገበ፤ በየቦታው እየሰፈሩ ያደረጉት ጒዞም ይህ ነው፤
3 እስራኤላውያን በመጀመሪያው ወር በዐሥራ አምስተኛውም ቀን በፋሲካ ማግስት ከራምሴ ተነሡ፤ ግብፃውያን ሁሉ እያዩአቸውም በልበ ሙሉነት ተጓዙ።
4 በዚህ ጊዜ ግብፃውያን እግዚአብሔር (ያህዌ) ከመካከላቸው የገደለባቸውን በኵሮቻቸውን ይቀብሩ ነበር፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) በግብፅ አማልክት ላይ ፈርዶ ነበር።
5 እስራኤላውያን ከራምሴ ተነሥተው በሱኮት ሰፈሩ።
6 ከሱኮትም ተነሥተው በምድረ በዳው ዳርቻ በምትገኘው በኤታም ሰፈሩ።
7 ከኤታም ተነሥተው ከበኣልዛፎን በስተ ምሥራቅ ወዳለችው ወደ ፊሀሒሮት በመመለስ በሚግዶል አጠገብ ሰፈሩ።