1 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤
2 “ከሌዋውያን ወገን የቀዓት ዘር የሆኑትን በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው ቊጠሩ።
3 እንዲሁም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ለማገልገል የሚመጡትን ከሠላሳ እስከ አምሳ ዓመት የሆናቸውን ወንዶች ሁሉ ቊጠሩ።
4 “በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የቀዓታውያን ሥራ ንዋየ ቅዱሳቱን መጠበቅ ነው።
5 ሰፈሩ ሲነሳ አሮንና ልጆቹ ገብተው የሚከልለውን መጋረጃ ያውርዱ፤ የምስክሩንም ታቦት ይጠቅልሉበት፤
6 ከዚያም በአቆስጣው ቍርበት ይሸፍኑት፤ ሙሉ በሙሉ ሰማያዊ የሆነ መጐናጸፊያ በላዩ ላይ ይዘርጉበት፤ መሎጊያዎቹንም በየቦታው ያስገቡ።
7 “በኅብስተ ገጹ ገበታ ላይ ሰማያዊ ጨርቅ ይዘርጉበት፤ በላዩም ላይ ወጭቶች፣ ጭልፋዎች፣ ጽዋዎች፣ ለመጠጥ ቍርባን የሚሆኑትን ማንቈርቈሪያዎች እንዲሁም ሁል ጊዜ ከዚያ የማይታጣውን ኅብስት ያስቀምጡ።