1 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
2 “እስራኤላውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፣ ‘ወንድም ሆነ ሴት ናዝራዊ ይሆን ዘንድ ራሱን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ለመለየት ስእለት ቢሳል፣
3 ከወይን ጠጅና ከሌላም ከሚያሰክር መጠጥ ይታቀብ፤ የወይንም ሆነ የሚያሰክር የሌላ መጠጥ ኾምጣጤ አይጠጣ፤ እንዲሁም የወይን ጭማቂ አይጠጣ፤ የወይን ፍሬም ሆነ ዘቢብ አይብላ።
4 በናዝራዊነቱ ወቅት ከወይን ተክል የሚገኘውን ማንኛውም ነገር፣ የወይኑን ዘር፣ ግልፋፊውንም እንኳ ቢሆን አይብላ።
5 “ ‘ስእለት ተስሎ ራሱን በለየበት ጊዜ ሁሉ ምላጭ ራሱን አይንካው፤ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተለየበት ጊዜ እስኪያበቃ ድረስ የተቀደሰ ይሁን፤ የራስ ጠጒሩንም ያሳድግ።