2 “እስራኤላውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፣ ‘ወንድም ሆነ ሴት ናዝራዊ ይሆን ዘንድ ራሱን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ለመለየት ስእለት ቢሳል፣
3 ከወይን ጠጅና ከሌላም ከሚያሰክር መጠጥ ይታቀብ፤ የወይንም ሆነ የሚያሰክር የሌላ መጠጥ ኾምጣጤ አይጠጣ፤ እንዲሁም የወይን ጭማቂ አይጠጣ፤ የወይን ፍሬም ሆነ ዘቢብ አይብላ።
4 በናዝራዊነቱ ወቅት ከወይን ተክል የሚገኘውን ማንኛውም ነገር፣ የወይኑን ዘር፣ ግልፋፊውንም እንኳ ቢሆን አይብላ።
5 “ ‘ስእለት ተስሎ ራሱን በለየበት ጊዜ ሁሉ ምላጭ ራሱን አይንካው፤ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተለየበት ጊዜ እስኪያበቃ ድረስ የተቀደሰ ይሁን፤ የራስ ጠጒሩንም ያሳድግ።
6 ራሱን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በለየበት ጊዜ ሁሉ ወደ ሬሳ አይቅረብ።
7 ራሱን ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም) የለየበት ምልክት በራሱ ላይ ስላለ አባቱም ይሁን እናቱ፣ ወንድሙም ይሁን እኅቱ ቢሞቱ ለእነርሱ ሲል እንኳ ራሱን አያርክስ።
8 ራሱን በለየበት ጊዜ ሁሉ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተቀደሰ ነው።