10 ቍጥራቸው እንዳይጨምር፣ ጦርነት ቢነሣ ከጠላቶቻችን ጋር አብረው እንዳይወጉንና ከምድሪቱም ኮብልለው እንዳይሄዱ ዘዴ እንፈልግ።”
11 ስለዚህ እያስጨነቁ የግዳጅ ሥራ የሚያሠሯቸውን አሠሪ አለቆች ሾሙባቸው። እስራኤላውያንም ፊቶምና ራምሴ የተባሉ ንብረት ማከማቻ ከተሞችን ለፈርዖን ሠሩለት።
12 ነገር ግን ባስጨነቋቸው መጠን የእስራኤላውያን ቍጥር በዛ፤ በምድሪቱም እየተስፋፉ ሄዱ፤ ከዚህም የተነሣ ግብፃውያኑ እስራኤላውያንን እጅግ ፈሯቸው፤
13 ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታም ያሠሯቸው ጀመር።
14 ጭቃ በማስቦካት፣ ጡብ በማሠራትና በእርሻም ሁሉ እያስጨነቁ ከባድ ሥራ እንዲሠሩ በማድረግ ሕይወታቸውን አስመረሩ፤ ግብፃውያኑ በሚያሠሯቸው ከባድ ሥራ ሁሉ ፈጽሞ አይራሩላቸውም ነበር።
15 የግብፅም ንጉሥ ሲፓራና ፉሐ የተባሉትን ዕብራውያን ሴቶች አዋላጆች እንዲህ አላቸው፤
16 “የዕብራውያንን ሴቶች በማማጫው ድንጋይ ላይ በምታዋልዱበት ጊዜ የሚወለደው ሕፃን ወንድ ከሆነ ግደሉት፤ ሴት ከሆነች ግን በሕይወት ትኑር።”