ዘፀአት 18:15-21 NASV

15 ሙሴም እንዲህ ብሎ መለሰለት፤ “ምክንያቱም ሰዎቹ የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ፈቃድ በመፈለግ ወደ እኔ ይመጣሉ።

16 ክርክር በኖራቸው ቍጥር ጒዳያቸው ወደ እኔ ይመጣል፤ ለግራና ለቀኙ የሚሆነውን እኔ ወስኜ የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ሥርዐትና ሕጎች እነግራቸዋለሁ።”

17 የሙሴ አማት መልሶ እንዲህ አለው። “የምትሠራው መልካም አይደለም።

18 አንተና ወደ አንተ የሚመጡት እነዚህ ሰዎች የምታደርጉት ነገር ቢኖር ራሳችሁን ማድከም ነው፤ ሥራው ለአንተ ከባድ ሸክም ነው፤ ብቻህን ልትወጣው አትችልም።

19 ምክር እሰጥሃለሁና አሁን እኔን አድምጠኝ፤ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ከአንተ ጋር ይሁን። አንተ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ፊት (የሕዝብ ተወካይ መሆን አለብህ)፤ ክርክራቸውን ወደ እርሱ ታቀርባለህ።

20 ሥርዐቶቹንና ሕጎቹን አስተምራቸው፤ እንዴት መኖር እንዳለባቸውና ምን መሥራት እንደሚገባቸው አሳያቸው።

21 ነገር ግን ችሎታ ያላቸውን ሰዎች ከሕዝቡ ሁሉ ምረጥ፤ እነዚህም ሰዎች እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) የሚፈሩ፣ ታማኞችና በማታለል የሚገኘውን ጥቅም የሚጸየፉ ይሁኑ። የሺህ፣ የመቶ፣ የአምሳ፣ የዐሥር፣ አለቃ አድርገህ ሹማቸው።