ዘፀአት 3:8-14 NASV

8 ስለዚህም ከግብፃውያን እጅ ልታደጋቸውና ማርና ወተት ወደምታፈሰው ሰፊና ለም ወደሆነችው ወደ ከነዓናውያን፣ ኬጢያውያን፣ አሞራውያን፣ ፌርዛውያን፣ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን ምድር ላወጣቸው ወርጃለሁ።

9 አሁንም የእስራኤል ልጆች ጩኸት ወደ እኔ ደርሷል፤ ግብፃውያን የሚያደርሱባቸውን ግፍ አይቻለሁ።

10 በል እንግዲህ ና፤ ሕዝቤን፣ የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ምድር እንድታወጣቸው ወደ ፈርዖን እልክሃለሁ”።

11 ሙሴ እግዚአብሔርን (ኤሎሂም)፣ “ወደ ፈርዖን የምሄድና የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ የማወጣ እኔ ማን ነኝ? አለው።

12 እግዚአብሔርም (ኤሎሂም)፣ “እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ እኔ የላክሁህ ለመሆኑ ምልክቱ ይህ ነው፤ ሕዝቡን ከግብፅ ካወጣሃቸው በኋላ በዚህ ተራራ ላይ እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ታመልካላችሁ” አለው።

13 ሙሴም እግዚአብሔርን (ኤሎሂም)፣ “ወደ እስራኤል ልጆች ሄጄ፣ ‘የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ልኮኛል’ ስላቸው ‘ስሙ ማን ነው?’ ብለው ቢጠይቁኝ ምን እላቸዋለሁ?” አለው።

14 እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ሙሴን፣ “እኔ፣ ያለሁና የምኖር ነኝ (ያህዌ)፤ ስለዚህም፣ ‘ያለና የሚኖር’ ልኮኛል ብለህ ንገራቸው” አለው።