ዘፀአት 33:11-17 NASV

11 ሰው ከባልንጀራው ጋር እንደሚነጋገር እግዚአብሔር (ያህዌ) ከሙሴ ጋር ፊት ለፊት ይነጋገር ነበር፤ ከዚያም ሙሴ ወደ ሰፈሩ ይመለሳል፤ ረዳቱ የነበረው ብላቴናው የነዌ ልጅ ኢያሱ ግን ከድንኳኑ አይለይም ነበር።

12 ሙሴ እግዚአብሔርን (ያህዌ) አለው፤ “ ‘እነዚህን ሕዝብ ምራ’ ብለህ ነግረኸኝ ነበር፤ ከእኔ ጋር የምትልከው ማን እንደሆነ ግን አላሳወቅኸኝም፤ ‘አንተን በስም አውቅሃለሁ፤ በፊቴም ሞገስ አግኝተሃል’ ብለህ ነበር።

13 በእኔ ደስ ተሰኝተህ ከሆነ፣ አንተን ዐውቅህና ያለ ማቋረጥ በፊትህ ሞገስ አገኝ ዘንድ መንገድህን አስተምረኝ፤ ይህ ሕዝብ የአንተ ሕዝብ መሆኑን አስታውስ።”

14 እግዚአብሔር (ያህዌ) “ሀልዎቴ ከአንተ ጋር ይሄዳል፤ ዕረፍትም እሰጥሃለሁ” ብሎ መለሰ።

15 ከዚያም ሙሴ እንዲህ አለው፤ “ሀልዎትህ ከእኛ ጋር ካልሄደ ከዚህ አትስደደን።

16 አንተ ከእኛ ጋር ካልሄድህ፣ አንተ በእኔና በሕዝብህ መደሰትህን ሌላው እንዴት ያውቃል? እኔንና ሕዝብህንስ በገጸ ምድር ከሚገኙት ከሌሎቹ ሕዝቦች ሁሉ ልዩ የሚያደርገን ሌላ ምን አለ?”

17 እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን፣ “በአንተ ደስ ስላለኝና በስም ስለማውቅህ፣ የጠየቅኸውን ያንኑ አደርጋለሁ” አለው።