ዘፀአት 34:1-7 NASV

1 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤ “እንደ መጀመሪያዎቹ ያሉ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ጥረብ፤ እኔም አንተ በሰበርካቸው በመጀመሪያዎቹ ጽላቶች ላይ የነበሩትን ቃሎች እጽፍባቸዋለሁ።

2 በማለዳ ተዘጋጅተህ ወደ ሲና ተራራ ውጣ፤ በዚያ በተራራው ጫፍ ላይ በፊቴ ቁም፤

3 ከአንተ ጋር ማንም እንዳይመጣ ወይም በተራራው ላይ በየትኛውም ቦታ እንዳይታይ፤ የበግና የፍየል መንጋዎች የቀንድ ከብቶችም እንኳ፣ በተራራው ፊት ለፊት መጋጥ የለባቸውም።”

4 ስለዚህ ሙሴ እንደ መጀመሪያዎቹ ያሉ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ጠርቦ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዘው በማለዳ ወደ ሲና ተራራ ወጣ፤ ሁለቱን የድንጋይ ጽላቶችም በእጆቹ ያዘ።

5 ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) በደመና ወረደ፤ በዚያም ከእርሱ ጋር ቆሞ ስሙን እግዚአብሔርን (ያህዌ) ዐወጀ።

6 እርሱም በሙሴ ፊት እንዲህ እያለ እያወጀ አለፈ፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ሩኅሩኅ ቸር አምላክ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩና ታማኝነቱ የበዛ፣

7 ፍቅርን ለሺዎች የሚጠብቅ፣ ክፋትን፣ ዐመፅንና ኀጢአትን ይቅር የሚል በደለኛውን ግን ሳይቀጣ ዝም ብሎ አይተውም፤ በአባቶች ኀጢአት ልጆችን የልጅ ልጆቻቸውን እስከ ሦስትና አራት ትውልድ ይቀጣል።”