8 ሙሴም ወዲያውኑ ወደ መሬት ዝቅ ብሎ ሰገደ፤
9 “አቤቱ ጌታ (አዶናይ) ሆይ፤ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ፣ ጌታ (አዶናይ) ከእኛ ጋር ይሂድ፤ ይህ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ቢሆንም እንኳ፣ ክፋታችንንና ኀጢአታችንን ይቅር በል፤ እንደ ርስትህም አድርገህ ውሰደን።”
10 ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ አለ፤ “ከአንተ ጋር ኪዳን እገባለሁ፤ ከዚህ ቀደም በዓለም ሁሉ ለየትኛውም ሕዝብ ከቶ ያልተደረገ፣ በሕዝብህ ሁሉ ፊት ድንቅ አደርጋለሁ፤ በመካከላቸው አብረሃቸው የምትኖር ሕዝብ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለአንተ የማደርግልህ ሥራ የቱን ያህል አስፈሪ እንደሆነ ያያሉ።
11 ዛሬ የማዝህን ፈጽም፤ አሞራውያንን፣ ከነዓናውያንን፣ ኬጢያውያንን፣ ፌርዛውያንን፣ ኤዊያውያንንና ኢያቡሳውያንን በፊትህ አስወጣቸዋለሁ።
12 ከምትሄድበት አገር ነዋሪዎች ጋር ቃል ኪዳን እንዳታደርግ ተጠንቀቅ፤ አለዚያ በመካከልህ ወጥመድ ይሆኑብሃል።
13 መሠዊያዎቻቸውን ሰባብሩ፤ የማምለኪያ ዐምዶቻቸውን አድቅቁ፤ የአሼራ ዐፀዶቻቸውንም ቍረጡ።
14 ስሙ ቀናተኛ የሆነው እግዚአብሔር (ያህዌ) ቀናተኛ አምላክ (ኤሎሂም) ነውና ሌላ አምላክ አታምልክ።