33 በወጋግራዎቹ መካከል ከዳር እስከ ዳር እንዲዘረጋ ሆኖ መካከለኛውን አግዳሚ ሠሩ።
34 ወጋግራዎቹን በወርቅ ለበጧቸው፤ አግዳሚዎቹን ለመያዝም የወርቅ ቀለበቶችን ሠሩ፤ እንዲሁም አግዳሚዎቹን በወርቅ ለበጧቸው።
35 ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ፣ በእጅ ጥበብ ባለ ሙያ ኪሩቤል የተጠለፉበት መጋረጃ አበጁ።
36 ለእርሱም አራት ምሰሶዎች ከግራር ዕንጨት ሠርተው በወርቅ ለበጧቸው፤ ለእነርሱም አራት የወርቅ ኵላቦችንና አራት የብር መቆሚያዎችን አበጁላቸው።
37 በድንኳኑ መግቢያ ጥልፍ ጠላፊ እንደሚሠራው ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ መጋረጃ አበጁለት፤
38 ለእነርሱም ኵላቦች ያሏቸው አምስት ምሰሶዎች ሠሩላቸው፤ የምሰሶዎቹን አናቶችና ዘንጎች በወርቅ በመለበጥ አምስቱን መቆሚያዎች ከነሓስ ሠሩ።