18 በአባይ ወንዝ ውስጥ ያለው ዓሣ ይሞታል፤ ወንዙ ይከረፋል፤ ግብፃውያንም ውሃውን መጠጣት አይችሉም።’ ”
19 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤ “አሮንን፣ ‘በትርህን ውሰድና በግብፅ ውሆች ላይ፣ ይኸውም በምንጮች፣ በቦዮች፣ በኩሬዎችና በውሃ ማጠራቀሚያዎች ላይ እጅህን ዘርጋ’ ብለህ ንገረው፤ ወደ ደምም ይለወጣሉ። ከእንጨትና ከድንጋይ በተሠሩ ውሃ መያዣዎች ውስጥም ሳይቀር በግብፅ ምድር ደም በየቦታው ይሆናል።”
20 ሙሴና አሮን እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ አዘዛቸው አደረጉ። እርሱም በንጉሡና በሹማምንቱ ፊት በትሩን አንሥቶ የአባይን ወንዝ ውሃ መታ። ውሃውም በሙሉ ወደ ደም ተለወጠ።
21 በአባይ ያሉት ዓሦች ሞቱ፤ ወንዙም ከመከርፋቱ የተነሣ ግብፃውያኑ ውሃውን ሊጠጡት አልቻሉም። በግብፅ ምድር ሁሉ ደም ነበረ።
22 የግብፅ አስማተኞች በድብቅ ጥበባቸው ተመሳሳይ ነገር አደረጉ፤ የፈርዖንም ልብ ደነደነ፤ ልክ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ተናገረው ሙሴንና አሮንን አልሰማቸውም።
23 ተመልሶ ወደ ቤተ መንግሥቱ ገባ እንጂ ይህንን ከቍም ነገር አልቈጠረውም።
24 ግብፃውያን ሁሉ የወንዙን ውሃ መጠጣት ባለመቻላቸው ውሃ ለማግኘት የአባይን ዳር ይዘው ጒድጓድ ቈፈሩ።