ዘፍጥረት 33:5-11 NASV

5 ከዚያም ዔሳው ቀና ብሎ ሲመለከት ሴቶቹንና ልጆቹን አየ፤ እርሱም፣ “እነዚህ አብረውህ ያሉት እነማን ናቸው?” ብሎ ጠየቀው።ያዕቆብም መልሶ፣ “እነዚህማ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በቸርነቱ ለእኔ ለአገልጋይህ የሰጠኝ ልጆች ናቸው” አለው።

6 በዚህ ጊዜ ሁለቱ ሴት አገልጋዮችና ልጆቻቸው ቀርበው እጅ ነሡ፤

7 ከዚያም ልያና ልጆቿ መጥተው እጅ ነሡ፤ በመጨረሻም ዮሴፍና ራሔል መጡ፤ እነርሱም ቀርበው እጅ ነሡ።

8 ዔሳውም፣ “ወደ እኔ ተነድቶ የመጣው ይህ ሁሉ መንጋ ምንድን ነው?” አለው።እርሱም፣ “ጌታዬ ሆይ፤ በአንተ ዘንድ ሞገስ ባገኝ ብዬ ነው” አለው።

9 ዔሳው ግን፣ “ወንድሜ ሆይ፤ እኔ በቂ አለኝ፤ የራስህን ለራስህ አድርገው አለው።

10 ያዕቆብም፣ “የለም፣ እንዲህ አይደለም፤ በአንተ ዘንድ ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ፣ እጅ መንሻዬን ተቀበል፤ በመልካም ሁኔታ ተቀብለኸኝ ፊትህን ማየት መቻሌ ራሱ፣ የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ፊት የማየት ያህል እቈጥረዋለሁ።

11 እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በቸርነቱ አሟልቶ ስለ ሰጠኝ የሚያስፈልገኝ ሁሉ አለኝና ያቀረብኹልህን እጅ መንሻ እባክህ ተቀበለኝ” አለው። ያዕቆብ አጥብቆ ስለ ለመነው፣ ዔሳው እጅ መንሻውን ተቀበለ።