8 “ወደ ማንኛውም ከተማ ስትገቡ ሰዎቹ ከተቀበሏችሁ፣ ያቀረቡላችሁን ብሉ።
9 በዚያ የሚገኙትን በሽተኞች እየፈወሳችሁ፣ ‘የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ቀርባለች’ በሏቸው።
10 ነገር ግን ወደ አንድ ከተማ ገብታችሁ ካልተቀበሏችሁ፣ ወደ አደባባዩ ውጡና እንዲህ በሉ፤
11 ‘በእግራችን ላይ ያለውን የከተማችሁን ትቢያ እንኳ እናራግፍላችኋለን፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ቀረበች ይህን ዕወቁ።’
12 እላችኋለሁ፤ በዚያን ዕለት ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶም ቀላል ይሆንላታል።
13 “ወዮልሽ ኮራዚን! ወዮልሽ ቤተ ሳይዲ በእናንተ የተደረገው ታምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን ኖሮ፣ ገና ዱሮ ማቅ ለብሰው፣ ዐመድ ነስንሰው ንስሓ በገቡ ነበር።
14 ነገር ግን በፍርድ ጊዜ ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል።