27 “እስቲ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ ተመልከቱ፤ አይለፉም፤ አይፈትሉም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ሰሎሞን እንኳ በዚያ ሁሉ ክብሩ ከእነርሱ እንደ አንዷ አልለበሰም።
28 እንግዲህ እግዚአብሔር ዛሬ ታይቶ ነገ ወደ እሳት የሚጣለውን የሜዳ ሣር እንዲህ የሚያለብስ ከሆነ፣ እናንተ እምነት የጐደላችሁ፣ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁም?
29 ስለዚህ ምን እንደምትበሉና ምን እንደምትጠጡ በመሻት ልባችሁ አይጨነቅ፤
30 ይህንማ በዓለም ያለ ሕዝብ ሁሉ ይፈልጋል፤ አባታችሁ እኮ ይህ ሁሉ እንደሚያስፈልጋችሁ ያውቃል።
31 ይልቁንስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ፈልጉ፤ ይህም ሁሉ በተጨማሪ ይሰጣችኋል።
32 “እናንተ አነስተኛ መንጋ የሆናችሁ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ መልካም ፈቃድ ነውና አትፍሩ፤
33 ያላችሁን ሽጡና ለድኾች ስጡ፤ ሌባ በማይሰርቅበት፣ ብል በማይበላበት፣ በማያረጅ ከረጢት የማያልቅ ንብረት በሰማይ አከማቹ፤