11 ምክንያቱም ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይላል፤ ራሱንም ዝቅ ዝቅ የሚያደርግ ሁሉ ከፍ ይላል።”
12 ኢየሱስም የጋበዘውን ሰው ደግሞ እንዲህ አለው፤ “የምሳ ወይም የእራት ግብዣ በምታደርግበት ጊዜ፣ በአጸፋው እንዳይጋ ብዙህና ብድራትን እንዳይመልሱልህ፣ ወዳጆችህን ወይም ወንድሞችህን ወይም ዘመዶችህን ወይም ከበርቴ ጐረቤቶችህን አትጋብዝ።
13 ነገር ግን ግብዣ ባዘጋጀህ ጊዜ ድኾችን፣ አካለ ስንኩሎችን፣ ሽባዎችንና ዐይነ ስወሮችን ጥራ፤
14 ትባረካለህም። እነዚህ ብድር ሊመልሱልህ ስለማይችሉ፣ በጻድቃንም ትንሣኤ ብድራትህ ይመለስልሃል።”
15 ከኢየሱስ ጋር በማእድ ከተቀመጡት መካከል አንዱ ይህን ሰምቶ “በእግዚአብሔር መንግሥት ቀርቦ ከማእድ የሚበላ ብፁዕ ነው” አለው።
16 ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “አንድ ሰው ትልቅ ግብዣ አዘጋጅቶ ብዙ ሰው ጠራ፤
17 የግብዣውም ሰዓት በደረሰ ጊዜ የተጋበዙትን እንግዶች፣ እነሆ፤ ሁሉም ነገር ተዘጋጅቶአልና ኑ ብሎ እንዲጠራ አገልጋዩን ላከባቸው።