1 ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፤ “አንድ ሀብታም ሰው አንድ መጋቢ ነበረው፤ ይኸው መጋቢ የሀብታሙን ሰው ንብረት እንደሚያባክን ለዚሁ ሀብታም ሰው ወሬ ደረሰው።
2 ስለዚህ አስጠራውና፣ ‘ይህ የምሰማብህ ምንድን ነው? ከእንግዲህ አንተ መጋቢ ልትሆነኝ ስለማትችል፣ የምታስተዳድረውን ንብረት መቈጣጠሪያ ሒሳብ አስረክበኝ’ አለው።
3 “መጋቢውም በልቡ እንዲህ አለ፤ ‘ጌታዬ ከመጋቢነት ሊሽረኝ ነው፤ ለማረስ ጒልበት የለኝም፤ መለመን ደግሞ ዐፍራለሁ፤ ስለዚህ ምን ላድርግ?
4 ከመጋቢነት የተሻርሁ እንደሆነ ሰዎች በቤታቸው እንዲቀበሉኝ የማደርገውን ዐውቃለሁ።’
5 “ስለዚህ የጌታው ዕዳ ያለባቸውን ሰዎች እያንዳንዳቸውን ጠራ፤ የመጀመሪያውንም ሰው ‘የጌታዬ ዕዳ ምን ያህል አለብህ?’ አለው።
6 “እርሱም፣ ‘አንድ መቶ ማድጋ ዘይት አለብኝ’ አለ። “መጋቢውም፣ ‘የውል ወረቀትህን እንካ፤ ቶሎ ተቀምጠህ “አምሳ ማድጋ” ብለህ ጻፍ’ አለው።
7 “ከዚያም ሌላውን፣ ‘አንተስ ስንት አለብህ?’ አለው። “እርሱም፣ ‘አምሳ ዳውላ ስንዴ’ አለው። “መጋቢውም፣ ‘የብድር ደብዳቤህን እንካ፤ “አርባ ዳውላ” ብለህ ጻፍ’ አለው።