ሉቃስ 3:1-7 NASV

1 ጢባርዮስ ቄሣር በነገሠ በዐሥራ አምስተኛው ዓመት፣ ይኸውም ጳንጥዮስ ጲላጦስ የይሁዳ ገዥ፣ ሄሮድስ የገሊላ አራተኛው ክፍል ገዥ፣ ወንድሙ ፊልጶስ የኢጡርያስና የጥራኮኒዶስ የአራተኛው ክፍል ገዥ ሊሳኒዮስም የሳቢላኒስ አራተኛው ክፍል ገዥ በነበሩበት ጊዜ፣

2 ሐናና ቀያፋም ሊቃነ ካህናት ሳሉ፣ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዘካርያስ ልጅ ወደ ዮሐንስ በምድረ በዳ መጣ።

3 እርሱም ለኀጢአት ስርየት የሚሆን የንስሓን ጥምቀት እየሰበከ በዮርዳኖስ ወንዝ አካባቢ ወዳሉት ስፍራዎች ሁሉ መጣ፤

4 ይኸውም ነቢዩ ኢሳይያስ በመጽሐፉ እንዲህ ሲል በጻፈው ቃል መሠረት ነበር፤“በበረሓ እንዲህ ብሎ የሚጮኽ ሰው ድምፅ፤‘የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤ጐዳናውንም አቅኑ፤

5 ሸለቆው ሁሉ ይሞላል፤ተራራውና ኰረብታው ሁሉ ዝቅ ይላል፤ጠማማው መንገድ ቀና፣ሸካራውም ጐዳና ትክክል ይሆናል፤

6 የሰውም ዘር ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ያያል።’ ”

7 ዮሐንስም በእርሱ እጅ ሊጠመቁ የወጡትን ሰዎች እንዲህ ይላቸው ነበር፤ “እናንት የእፉኝት ልጆች፣ ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን መከራችሁ?