2 በዚህ ጊዜ ሁለት ጀልባዎች በሐይቁ ዳርቻ ቆመው አየ፤ ዓሣ አጥማጆቹ ግን ከጀልባዎቹ ወርደው መረባቸውን ያጥቡ ነበር።
3 ከጀልባዎቹም መካከል የስምዖን ወደ ነበረችው ገብቶ፣ ከምድር ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጋት ለመነው፤ ከዚያም ጀልባዋ ላይ ተቀምጦ ሕዝቡን ያስተምር ጀመር።
4 ንግግሩን በጨረሰ ጊዜ ስምዖንን፣ “ወደ ጥልቁ ውሃ ፈቀቅ በልና ዓሣ ለመያዝ መረባችሁን ጣሉ” አለው።
5 ስምዖንም መልሶ፣ “መምህር ሆይ፤ ሌሊቱን ሙሉ ስንደክም አድረን ምንም አልያዝንም፤ አንተ ካልህ ግን መረቦቹን እጥላለሁ” አለው።
6 እንደዚያም ባደረጉ ጊዜ እጅግ ብዙ ዓሣ ያዙ፤ መረባቸውም ይበጣጠስ ጀመር።
7 በሌላ ጀልባ የነበሩት ባልንጀሮቻቸው መጥተው እንዲያግዟቸውም በምልክት ጠሯቸው፤ እነርሱም መጥተው ሁለቱን ጀልባዎች በዓሣ ሞሏቸው፣ ጀልባዎቹም መስመጥ ጀመሩ።
8 ስምዖን ጴጥሮስም ይህን ባየ ጊዜ በኢየሱስ ጒልበት ላይ ወድቆ፣ “ጌታ ሆይ፤ እኔ ኀጢአተኛ ሰው ነኝና ከእኔ ተለይ” አለው።