3 የሄሮድስ ቤት ኀላፊ የነበረው የኩዛ ሚስት ዮሐና፣ ሶስና፣ ደግሞም ሌሎች ብዙዎች ነበሩ፤ እነዚህም በግል ንብረታቸው የሚያገለግሉት ነበሩ።
4 ብዙ ሕዝብ በአንድነት ተሰብስቦ ሳለ፣ ደግሞም ሰዎች ከተለያዩ ከተሞች ወደ እርሱ በሚጐርፉበት ጊዜ፣ ይህን ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤
5 “አንድ ዐራሽ ዘሩን ሊዘራ ወጣ፤ ሲዘራም፣ አንዳንዱ ዘር መንገድ ዳር፤ ወደቀ በእግርም ተረጋገጠ፤ የሰማይ ወፎችም በሉት።
6 አንዳንዱም ዘር በድንጋያማ ቦታ ላይ ወደቀ፤ እንደ በቀለም ርጥበት አልነበረውምና ደረቀ።
7 ሌላው ዘር ደግሞ እሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም አብሮት አደገና አንቆ አስቀረው።
8 ሌላውም ዘር በመልካም መሬት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ መቶ ዕጥፍም አፈራ።”ይህን ብሎ ሲያበቃም ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ” አለ።
9 ደቀ መዛሙርቱም የዚህን ምሳሌ ትርጒም ጠየቁት።