ሮሜ 1:27-32 NASV

27 እንደዚሁም ወንዶች ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወት ተቃጠሉ፤ ወንዶች ከወንዶች ጋር ነውር ፈጸሙ፤ ለክፉ አድራጐታቸውም የሚገባቸውን ቅጣት በገዛ ራሳቸው ላይ አመጡ።

28 ከዚህም በላይ በሐሳባቸው እግዘአብሔርን ማወቅ አይጠቅምም በማለታቸው፣ መደረግ የማይገባውን እንዲያደርጉ እግዚአብሔር ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው።

29 በሁሉም ዐይነት ዐመፃ፣ ክፋት፣ ስግብግብነትና ምግባረ ብልሹነት ተሞልተዋል፤ ቅናትን፣ ነፍስ ገዳይነትን፣ ጥልን፣ አታላይነትንና ተንኰልን የተሞሉ ናቸው፤ ሐሜተኞች፣

30 ስም አጥፊዎች፣ አምላክን የሚጠሉ፣ ተሳዳቢዎች፣ ትዕቢተኞችና ትምክሕተኞች ናቸው፤ ክፋትን የሚሠሩበትን መንገድ ያውጠነጥናሉ፤ ለወላጆቻቸው አይታዘዙም።

31 የማያስተውሉ፣ ውል የሚያፈርሱ፣ ርኅራኄ የሌላቸውና ጨካኞች ናቸው።

32 ይህን የሚያደርጉ ሁሉ ሞት ይገባቸዋል የሚለውን ትክክለኛ የሆነውን የእግዚአብሔርን ሕግ ቢያውቁም፣ እነዚህን ነገሮች ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ እንዲህ የሚያደርጉትንም ያበረታታሉ።