2 ሴቲቱ ግን በታማኝነት አልጸናችም፤ ትታውም በይሁዳ ምድር ወደሚገኘው ወደ አባቷ ቤት ወደ ቤተ ልሔም ሄደች፤ እዚያም አራት ወር ከቈየች በኋላ፣
3 ባሏ ታርቆ ሊመልሳት ወደ እርሷ ሄደ፤ ሲሄድም አሽከሩንና ሁለት አህዮችን ይዞ ነበር፤ ሴቲቱም ወደ አባቷ ቤት አስገባችው፤ አባቷም ባየው ጊዜ በደስታ ተቀበለው።
4 የልጂቱ አባትም እዚያው እንዲቈይ አጥብቆ ለመነው፤ ስለዚህ እየበላ እየጠጣ ሦስት ቀን አብሮት ተቀመጠ።
5 በአራተኛው ቀን ማልደው ተነሡ፤ እንግዳውም ለመሄድ ተዘጋጀ፤ የልጂቱ አባት ግን፣ “እንድትበረታ እህል ቅመስ፤ ከዚያም መሄድ ትችላለህ” አለው።
6 ስለዚህ ሁለቱ ለመብላትና ለመጠጣት አብረው ተቀመጡ። የልጂቷም አባት፣ “እባክህ ዛሬም እዚሁ አድረህ ተደሰት” አለው።
7 ሰውየው ለመሄድ ሲነሣም ዐማቱ እንዲያድር ለመነውና እዚያው አደረ።
8 በአምስተኛውም ቀን ጠዋት ሌዋዊው ለመሄድ ሲነሣ፣ የልጂቱ አባት “ሰውነትህን አበርታ፤ ጥላው እስኪበርድም ድረስ በዚሁ ቈይ” አለው፤ ስለዚህ ሁለቱም አብረው በሉ።